Fana: At a Speed of Life!

በተደረጉ ድርድሮች የግብጽ ወገን አጀንዳዎችን እያቀረበ ውይይቱን ውጤት አልባ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ይመጣ ነበር- አቶ ገዱ

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ከግድቡ ጋር በተያያዘ ባደረጓቸው ድርድሮች የግብጽ ወገን የተለያዩ አጀንዳዎችን እያቀረበ ውይይቱን ውጤት አልባ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ይመጣ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለፁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከአልጀዚራ አረብኛ ስርጭት ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህ ወቅት እንደተናገሩ ግብጽ የራሷን ፍላጎት ብቻ ለመጫን ትሰራ እንደነበርም አስረድተዋል።

ግብጽ በጎረቤት ሀገሮች ላይ የጦር ካምፕ ለመመስረትና የኢትዮጵያን ደህንነት ለመፈታተን የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ግብጽ የተለያዩ መከራዎችን በመጠቀም ላይ መሆኗን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት በመሆኑ ሙከራው የማይሳካ ህልም ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም የጎረቤት ሀገሮች ግንኙነታቸውን በማጠናከር ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና ውህደት እያመሩ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ሲመዘን ሀገራቱ ግብጽን በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ይንቀሳቀሳሉ ብለው እንደማያምኑም አቶ ገዱ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠናከረ እንደመጣ የገለጹት አቶ ገዱ፤ ከእርሻ መሬት ጋር በተያያዘ በድንበር አካባቢ የሚነሳው ችግር ለዘመናት የቆየ በመሆኑ ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት ሁለቱ ሀገራት በጋራ እና በትብብር እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ የተከሰተውን ሰሞነኛ ክስተት የግብጽ ሚዲያዎች እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ በስፋት ሲሰሩ መቆየታቸውንም አቶ ገዱ መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

የግብጽ ሚዲያዎች ሃላይብ ትሪያንግል በመባል የሚታወቀውን የሱዳን መሬት ግብጽ በወረራ መያዟን በተመለከተ አንድም ቀን ሳይተነፍሱ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ጉዳይ እንደ ትልቅ አጀንዳ አንስተው ሰፊ ሽፋን መስጠታቸው ያላቸውን ተዓማኒነት ትዝብት ውስጥ ይከታልም ነው ያሉት።

ግብጾች ግድቡን ከእስራኤል ጋር ለማገናኘት መሞከራቸው ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀል መሆኑንም ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.