Fana: At a Speed of Life!

በህዳሴ ግድብ ዙርያ በግብፅ የሚደረገውን የዲፕሎማሲ ጫና እና የሴራ ፖለቲካ ለማክሰም የግድቡን ግንባታ በፍጥነት ማጠናቅቅ ወሳኝ  ነው- ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙርያ በግብፅ የሚደረገውን የዲፕሎማሲ ጫናና የሴራ ፖለቲካ እስከ መጨረሻው ለማክሰም የግድቡን ግንባታ በፍጥነት ማጠናቅቅ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የፖለቲካ እና የታሪክ ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራኑ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ የግድቡ ግንባታ በተፋጠነ ቁጥር ከካይሮ ሊሰነዘሩ የሚችሉ የአጅ አዙር የደህንነት ስጋቶችን ለመቀልበስ ሁለም ኢትዮጵያዊ በንቃት መጠበቅ ይገባዋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨረሲቲ የታሪክ ትምህርት ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ መኮንን፥ ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ ባጎረስኩ ተነከስኩ ብሂል እየተጓዘች ያለች ሀገር ናት ብለዋል።

ዶክተር ተፈሪ፥ የእስካሁኑን የዓባይ ወንዝ ፖለቲካ ኢፍትሃዊ አካሄድ መቀልበስ የሚቻለው ግድቡን በማጠናቀቅ ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ የካይሮን የዘመናት የናይል ወንዝ ለብቻዬ ልጠቀም የጥቅላላ ውሃ ፖለቲካ ለማስተካከል የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቅፍ እንዲመሰረት አድርጋለች ነው ያሉት።

ይህ ማዕቀፍ ግን በካይሮ ሰዎች አሳሳች ዲፕሎማሲ እና ኢትዮጵያን አግላይ ስልት ከተገቢው ደረጃ አልደረሰም።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ እና በብሉ ናይል የውሃ ምርምር ማዕከል የውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ውብእግዜር ፈረደ፥  የግብፅ አካሄድ የመስኖ ስራዬ ይጎዳል አልያም ግድቡ የከፋ ተፅእኖ ያደርሳል ከሚል አመክንዮ የመጣ አይደለም ነው የሚሉት።

አቶ ውብ እግዜር ፈረደ እንደሚሉት፥ የዓባይ ወንዝን የፖለቲካ ካርድ መምዘዣ ማድረግን ማስቆም ይገባናል ባይ ናቸው።

ዶክተር ተፈሪ መኮንን ደግሞ፥ በህብረተሰቡ ዘንድ በህዳሴው ግድብ ዙርያ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ግንዛቤ እንዲፈጠር መሰራት ያለበት ጉዳይ አለ ባይ ናቸው።

በስላባት ማናዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.