Fana: At a Speed of Life!

በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ዜጎች አያያዝ ሊገመገም ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ዜጎችን አያያዝ ከነገ ጀምሮ ሊገመግም ነው።

በዚህም መንግስት ለዜጎች የሰጠው ትኩረት እና ዜጎች ያሉበት አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሁም ከሰብዓዊ መብት አንጻር ምልከታ እንደሚደረግ መርማሪ ቦርዱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ገልጿል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመቆጣጠርም ቦርዱ ክትትል እያደረኩ ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመቆጣጠር መንግስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም የሚከታተል መርማሪ ቦርድ መቋቋሙ ይታወቃል።

ቦርዱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ወቅት የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ተከታትሎ በህግ ፊት ማቅረብ፥ በዚህ ምክንያት ወደ ማረሚያ የሚገቡ ካሉም ከታሰሩበት ተገቢነት አንጻር በመመልከት የምርመራ ውጤቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ ሃላፊነት አለበት።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት፥ በህብረተሰቡ ዘንድ ቸልተኝነት እንደሚታይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ዜጎች የወጡ ህጎችን ለራሳቸው ሲሉ በማክበር ጤናቸውን እንዲጠብቁ እና ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ህግን በማክበር ንትርክ ውስጥ መግባት እንዳይገቡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.