Fana: At a Speed of Life!

በላፍቶ የአትክልት እና ፍራፍሬ የገበያ ማዕከል የተረጋጋ የግብይት እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ መሆኑን ነጋዴዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ዘመናዊ የአትክልት እና ፍራፍሬ የገበያ ማዕከላት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ገለፀ ።

ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች አዲሱን የላፍቶ የአትክልት እና ፍራፍሬ የገበያ ማዕከል የንግድ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ በጃንሜዳ የነበረውን ጊዜያዊ በመዝጋት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ላፍቶ አካባቢ አዲስ እና ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ማዕከል በአጭር ጊዜ በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።

ከገበያ ማዕከሉ ጉብኝት በኃላ ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ በአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም አጠቃላይ የግብይት እንቅስቃሴውን ስርዓት ለማስያዝ በርካታ ስራዎች እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ በእቅድ ከያዛቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የገበያ ማዕከላትን ዘመናዊና ተደራሽ ማድረግ አንዱ ነው ያሉት አቶ አብዱልፈታህ አዲሱን የላፍቶ የአትክልትና ፍራፍሬ ማዕከል የመሰሉ በተለያዩ አካባቢዎች ግዙፍ የገበያ ማዕከላት እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።

የገበያ ማዕከላት ሲገነቡ መሰረተ ልማቶች አስፈላጊ መሆናቸውን የገለጹት ሃላፊው፤ የላፍቶ የገበያ ማዕከል ሲገነባ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አውስተዋል።
የኤሌክትሪክ፣ የውሃና የመንገድ ችግሮች እንዳያጋጥሙ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው አካባቢውን በገበያ ማዕከሉ አገልግሎት ለሚሰጡ ነጋዴዎች ካፍቴሪያዎችና መጸዳጃ ቤቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል ።

በላፍቶ አትክልት እና ፍራፍሬ የገበያ ማዕከል ነጋዴዎች በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ በተለይ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች አመራሮች የገበያ ማዕከሉ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ባደረጉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል ።

በገበያ ማዕከሉ እየተካሄደ ያለው የግብይት እንቅስቃሴም የተረጋጋ መሆኑን ነጋዴዎቹ ተናግረዋል ።

የላፍቶ የገበያ ማዕከል ለችርቻሮ 504 ሱቆች ለጅምላ የሚሆኑ 52 በድምሩ 556 ማስተናገድ የሚችሉ ሲሆን ለማእከሉ ግንባታ ከአካባቢያቸው ለተነሱ 24 አርሶአደሮች እና ለባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ሁለት ቦታ እንዲያገኙ መደረጉን የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ አንድ ወር ባልሞላ ግዜ ውስጥ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የኃይሌ ጋርመንት አካባቢ ላፍቶ የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ማእከልን በ1 ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብ በ8ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የንግድ ማዕከሉን በማስገንባት በውስጡም በቂ የመኪና ማቆሚያና የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ ሱቆች፣ የምግብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎችና የንፅህና መጠበቂያ ስፍራን መገንባት ተችሏል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.