Fana: At a Speed of Life!

በመቐለ ለነዋሪዎች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መቐለ ከተማ የደረሰው የእለት ደራሽ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለዜጎች በመድረስ ላይ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ገለጸ።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሰብዓዊ ድጋፍ አሰተባባሪ ወይዘሮ ሳባ ገብረማርያም በመቀሌ ከተማ ለ80 ሺህ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የፌዴራል መንግስት በክልሉ የምግብ፣ መድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማቅረብ ላይ ሲሆን ጊዜያዊ አስተዳደሩም ለህዝቡ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ እህል በመጋዘን መኖሩን ጠቅሰው እርዳታና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች በመከፋፈል ላይ መሆኑን ወይዘሮ ሳባ ገልጸዋል።

በዚህም በመቀሌ ከተማ ብቻ ለ80 ሺህ ዜጎች ድጋፉን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰብአዊ ድጋፉን በክልሉ የተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች በመዳረስ ላይ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በርካታ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎችም በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን በመደገፍ ላሳዩት ተነሳሽነት አመስግነዋል።

ከፌዴራሉ መንግስት የተላከውን ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት መድሃኒትም ማሰራጨት መቻሉን ወይዘሮ ሳባ ገልጸዋል።

ከፌዴራል መንግስቱ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ እና አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በድጋፉ ማህበረ ረድኤት ትግራይ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና ከካቶሊክ ሪሊፍ ሶሳይቲ ጋር በመተባበር በመጠለያ ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ኢዚአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.