Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን ከተከሰተው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በ45 አመራሮች ላይ እርምጃ ሲወሰድ ከእነዚህም ውስጥ 10ሩ በህግ እንዲጠየቁ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ከተከሰተው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች ላይ ክልሉ ህጋዊና ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

በዚህም በ45 አመራሮች ላይ እርምጃ  የተወሰደ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንድ የአመራር ሽግሽግ ሲደረግ ሌሎቹ በሙሉ ከኃላፊነት እንዲነሱ ተወስኗል።

እንዲሁም ከመካከላቸው 10 አመራሮች በህግ እንዲጠየቁና ምርመራ እንዲጣራባቸው መደረጉን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በመሆኑም በክልል ደረጃ የክልሉ ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ ፣  የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ኮማንደር ወጋሪ ፖሊ ከሃላፊነት ሲነሱ  የሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊው አቶ አበራ ባየታ በሽግሽግ ወደ ሌላ ቢሮ ተዛውረዋል።

እንዲሁም የመተከል ዞን 8 አመራሮች ከሃላፊነት የተነሱ ሲሆን በወረዳ ደረጃም በቡለን   ፣ ወምበራ  ፣ ዳንጉር  ፣ ድባጢ  ፣ ማንዱራ እና ጉባ ወረዳዎች ሃላፊነታቸውን አልተወጡም የተባሉ አመራሮች ከሃላፊነት መነሳታቸው ተጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.