Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች ለምርጫው ከማለዳ ጀምሮ አገልግሎት ይሰጣሉ – ትራንስፖርት ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ለነገው ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች ከማለዳ ጀምሮ አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ይርጋለም ብርሃኔ እንደገለጹት፥ ለድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በመዲናዋ የትራንስፖርት እጥረት እንዳይከሰት የዝግጅት ስራዎች ቀደም ብለው ተከናውነዋል።

በእለቱ የትራንስፖረት አገልገሎት አሰጣጡን የሚከታተል፣ የሚመራና ከየዘርፉ የተውጣጣ ግብረ ሃይል መቋቋሙንም ገልጸዋል።

የታክሲ አሽከርካሪዎችና ማህበራት፤ የብዙሃን ትራንስፖርት አቅራቢ ድርጅቶች ማለትም አንበሳ፣ ሸገርና ሃይገር ባሶች፣ የላዳ ሾፌሮችና ማህበራት ጋር ውይይት በማድረግ የስራ መመሪያ ማስቀመጥ መቻሉን አብራርተዋል።

ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶችን በመጨመር አገልግሎቱ በተሳለጠ መልኩ እንዲሰጥ ይደረጋል ሲሉም አቶ ይርጋለም አረጋግጠዋል።

በዚህም በመዲናዋ ያሉ ሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የትራንሰፖርት እጥረት ይከሰትባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን በመለየት ተጨማሪ ስምሪቶች ይሰጣል መባሉን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በእለቱ የታክሲ አስተባባሪዎችና የትራንስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴዎች እጥረት ሲያጋጥም አፋጣኝ መፍትሄ የሚሰጡበት አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የትራፊክ ፖሊሶች፣ የደምብ ልብስ የለበሱ የቢሮው ባለሙያዎችና የተቋቋመው ኮሚቴ በቅንጅት የሚሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአንበሳ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት በእለቱ 665 አውቶብሶችን ለትራንስፖርት ዝግጁ ማድረጉንም አረጋግጠዋል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገበየሁ ዋቄ በከተማዋ የትራንሰርት አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንዲቻል የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ነው የገለጹት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.