Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ለጥቃት የተጋለጡ ሴቶች እና ህጻናትን የመለየት ስራ ይሰራል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ በቅርቡ ተግባራዊ በተደረገው መንደርን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት ለጥቃት የተጋለጡ ሴቶች እና ህጻናትን የመለየት ስራ እንደሚሰራ የከተማው ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ፣የፍትህ እና ጸጥታ ተቋማት የሴቶች እና የህጻናት ጥቃትን ለመከላከል እንዲሁም ጥቃት አድራሾች ላይ በሚወሰደው እርምጃ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ አብረሃ÷በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ሳቢያ በከተማዋ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት መልኩን እየቀየረ በመጨመር ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመዲናዋ በቅርቡ ተግባራዊ በተደረገው መንደርን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት ለጥቃት የተጋለጡ ሴቶች እና ህጻናትን የመለየት ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ህብረተሰቡም በየአካባቢው ጥቃት አድራሾችን የማጋለጥ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ቢሮው ጥቃት አድራሾችን ለፍርድ ለማቅረብ ከጠቅላይ አቃቢ ህግ ቢሮ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

ከዚያም ባለፈ በተለያዩ ጊዜያት ለጥቃት የተጋለጡ ሴቶች እና ህጻናት ስነልቦናዊ ጫና እንዳይደርስባቸው የመንከባከብ በዘላቂነትም ድጋፍ አስተዳደሩ ድጋፍ የሚያደርግበት ሁኔታ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ወይዘሮ አልማዝ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው ÷መላው ህብረተሰብ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት የማውገዝ እና አስቀድሞ ለመከላከል ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባል ብለዋል፡፡

በሴቶች እና ህጻናት ጥቃት ጋር በተያያዘ ባለፉት 9 ወራት በከተማዋ ከ349 በላይ ጥቆማዎች ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቀርበው ከ209 በላዩ በአቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶ በፍርድ ሂደት ላይ ሲሆን 89 ደግሞ በፖሊስ ምርመራ እንዲሁን በ12 ላይ ውሳኔ መተላለፉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.