Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በ2011 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ወጥቶላቸው ቁልፍ ላልተረከቡ እድለኞች ቁልፍ የማስረከቡ ስራ በአፋጣኝ እንደሚፈፀም ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ በየካቲት 27-2011 ዓ.ም በተደረገው ዕጣ ማውጣት ስነ-ስርአት ዕጣ ወጥቶላቸው ውል ላልገቡ እና ቁልፍ ላልተረከቡ ባለ ዕጣዎች ውል ማስገባትና ቁልፍ ማስረከቡ በአፋጣኝ እንዲፈፀም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገለፀ።
 
የከተማ አስተዳደሩ በየወቅቱ የሚነሱ የነዋሪዎቹን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በመግለፅ ከእነዚህም ውስጥ የጋራ መኖርያ ቤቶች ጉዳይ አንዱና የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ የበዛበት ሆኖ መቆየቱን አመልክቷል።
 
በተደረገው ማጣራት እና የስራ ሪፖርት መሰረት ዕጣ ወጥቶላቸው ለባለ ዕጣዎች እጅ ያልደረሱ ቤቶች መኖራቸው ታውቋል ብሏል፡፡
 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ40/60 እና 20/80 ፕሮግራሞች የተገነቡ ቤቶችን የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ዕጣ ማውጣቱ የተገለፀ ሲሆን ሆኖም ቤቶቹ በቂ የመሠረተ ልማት በሌለባቸው የማስፋፊያ አካባቢዎች በመገንባታቸው እና በሚፈለገው ልክ አጠቃላይ የሳይት ስራው በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ለባለ እድለኞች ሳይተላለፉ መቆየታቸውን የከተማው አስተዳደር በመረዳቱ እጣ ወቶላቸው ውል ላልገቡ እና ቁልፍ ላልተረከቡ ባለ ዕጣዎች ውል ማስገባትና ቁልፍ ማስረከቡ በአፋጣኝ እንዲፈፀም አስታውቋል።
 
በመሆኑም በ20/80 ፕሮግራም የዕጣው አሸናፊ ሆነው ውል ላልፈጸሙ 32 ሺህ 653 ባለ እድለኞች ውል ማዋዋሉ የተጀመረ ሲሆን በቅርቡ ቁልፍ የሚረከቡ መሆኑን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
 
በ40/60 ፕሮግራም ከዚህ ቀደም ውል ለፈጸሙ 18 ሺህ 576 እድለኞች ቁልፍ የማስረከብ ስራ መጀመሩንም የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.