Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በ2013 ከ280 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራ የከተማ አስተዳደሩ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2013 በጀት ዓመት ከ280 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

ለስራ እድል ፈጠራ በብድር መልክ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በጀት መመደቡም ተገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት በስራ እድል ፈጠራ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማካሄዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሰክረተሪያት ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

በምክክር መድረኩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጅነር እንዳወቅ አብቴን ጨምሮ ከስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለቸው አስተግባሪ ተቋማት ተሳትፈዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችን እና ወጣቶችን በተለያዩ የስራ ዘርፎች በማሰማራት ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝም በመድረኩ ተገልጿል።

በተጀመረው በጀት ዓመትም የብድር እና የመስሪያ ቦታ አቅርቦት ችግሮች በመፍታት ለ280 ሺህ ያህል ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራም ነው የተገለፀው።

የስራ እድል ለመፍጠር የተያዘውን እቅድ ከግብ ለማድረስ ከመንግስት እና ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጀት ለመስራት ታሳቢ የተደረገ ሲሆን፥ በዚህም እድገት ተኮር በሆኑ በከተማ ግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድና አገልግሎት ዘርፎች ሰፊ ትኩረት እንደሚሰጠው ተጠቁሟል።

ለስራ እድል ፈጠራው የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም በብድር መልክ የከተማ አስተዳደሩ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በጀት ተመድቧል ነው የተባለው።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.