Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ባለፉት አምስት ወራት ለ118 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 17 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት አምስት ወራት ለ118 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩን የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይመር ከበደ ÷ባለፉት አምስት ወራት ለዜጎች በተለያዩ ዘርፎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት አምስት ወራት ለመፍጠር ከታቀደው 154 ሺህ የሥራ እድል ለ118 ሺህ ዜጎች ስራ ተፈጥሮላቸው ወደ ስራ መሰማራታቸውን አስረድተዋል።
ወጣቶች፣ ሴቶችና የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን መሰረት በማድረግ በግብርና፣ በማምረቻ፣ በንግድ፣ በአገልግሎትና ግንባታ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል ብለዋል።
የመሰረተ ልማት፣ የፋይናንስና የገበያ ትስስር በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችገሮች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የአገር ውስጥና የውጭ ገበያ በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች አይነተኛ ችግር መሆኑንም አንስተዋል።
ችግሩን ለመፍታት የመንገድ ዳርና የኦንላይን ግብይትን ጨምሮ የተለያዩ የገበያ አማራጮች እየተመቻቹ እንደሆነ አቶ ይመር ገልጸዋል።
ኢንተርፕራይዞች በቋሚነት በሳምንት ሁለት ቀን ሽያጭ የሚያደርጉበት አሰራር በመመቻቸት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም የመንገድ ዳር ባዛር ኢንተርፕራይዞቹ ምርታቸውን የሚያቀርቡበት በመሆኑ በስፋት እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።
ወደ ኦንላይን ግብይት ሥርአት የገቡ ኢንተርፕራይዞች ውጤት እያሳዩ በመሆኑ በዘላቂነት እንደሚሰራበት አስረድተዋል።
የሥራ እድል በተፈጠረበት በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ 154 ሚሊየን ብር ብድር ሥራ ለተፈጠረላቸው ዜጎች መሰጠቱን ኃላፊው ተናግረዋል።
በከተማዋ በዓመቱ ለ280 ሺህ ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን አስታውሰው በቀሪው ጊዜ ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚሰራ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.