Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያትም የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 19 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያትም የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

ተጠርጣሪው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ ጨው በረንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋሉን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ታሪኩ መንገሻ ተናግረዋል።

ግለሰቡ በሀሰተኛ መንገድ ካዘጋጃቸው መንጃ ፍቃዶች፣ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የተለያዩ ማህተሞች፣ ፓስፖርቶች፣ ቲተሮች፣ የልደት ካርዶች እና ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።

አንዳንድ ግለሰቦች በጥረታቸው ከሚያገኙት ብቃት ይልቅ በአቋራጭ መንገድ በመጠቀም ህገ-ወጥ ሰነዶችን በማሰራት ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መከሰት ምክንያት መሆናቸውን ሃላፊው አንስተዋል።

በተለይም መሰል ወንጀሎች እየተባባሰ ለመጣው የመንገድ ትራፊክ አደጋ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወንጀሉ ሀገርንና ትውልድን የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ ህብረተሰቡ አምርሮ ሊኮንነው እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.