Fana: At a Speed of Life!

በመጪው መስከረም ወር እምቦጭ አረምን ለማስወገድ የሚያስችል የዘመቻ ሥራ ይከናወናል – ም/ ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው መስከረም ወር እምቦጭ አረምን ለማስወገድ የሚያስችል የዘመቻ ሥራ እንደሚከናወን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የእምቦጭ አረምን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ በተዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት ውይይት ተደርጓበታል።

ስትራቴጂክ ዕቅዱ አረሙን ማስወገድ፣ በዘላቂነት የውኃና አካባቢ ጥበቃ መሥራትና ነፃ የሀይቅ ዳርቻ መሥራት እንዲሁም በሀይቁ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ዕቅዱ ላይ ገለጻ ያደረጉት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የእምቦጭ አረም በ1956 ዓ.ም በአባ ሣሙዔል ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ መጤ ወራሪ አረም መሆኑን ይገልጻሉ።

ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በጣና ሀይቅ ላይ አረሙ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን በአማራ ክልል በሚገኙ ሰባት ወረዳዎችና 35 ቀበሌዎች መዳረሱን ተናግረዋል።

እምቦጭ አረም በብዝሃ ሕይወት አንዲሁም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የደቀነው ሥጋት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በጣና ሀይቅና በአጠቃላይ በጣና ተፋፈስ ዙሪያ የእርሻ መስፋፋት፣ የውኃ አካላት ላይ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ ከከተማና ከኢንዱስትሪ ወደ ጣና ሀይቅ የሚገቡ ፍሳሾች አረሙ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

ይሁንና አረሙን ማስወገድ የሚቻለው ልማዳዊ ከሆነ አሰራር ወጥቶ ስትራቴጂውን ተግባራዊ በማድረግ መሆኑን በመግለፅ ለዚህም በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮች በማየት እምቦጭ አረምን ለኃይል አማራጭነት መጠቀም እንደሚቻል መግለፃቸውን ኢዜዘ ዘግቧል።

የእምቦጭ አረምን ለመከላከል በጣና ተፋፈስ ዙሪያ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በተለይም የተለያዩ ፈሳሾችና ንጥረ ነገሮች ወደ ሀይቁ እንዳይገቡ የማድረግ ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.