Fana: At a Speed of Life!

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተወሰነዉ የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ረቂቅ ፖሊሲ ሲብራራ  

የሚኒስትሮች ም/ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 80ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ስለተወሰነዉ የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ረቂቅ ፖሊሲ ተጨማሪ ማብራሪያ:-

እንደሚታወቀው አማርኛ የፌደራሉ የሥራ ቋንቋ በመሆኑ እርስ በእርሳችን እንድንግባባ በማደረግ ረገድ ሚናው ትልቅ ነው። አማርኛ ቋንቋ በሀገር ወስጥ ያለው የተናጋሪዎች ብዛትና የተደራሽነት ስፋት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አንድ የፓለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ተግባቦትን ለማሳለጥ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎችን መጠቀም አንዱ መንገድ ነው። ለዚህም በሀገር ውስጥ ያለውን ትሥሥር ከማጎልበት አልፈው ከጎረቤቶቻችን ጋር ጭምር የሚያስተሣሥሩንን ቋንቋዎች ከአማርኛ ጎን ለጎን ብንጠቀም ይበልጥ ተጠቃሚ እንሆናልን። ይሄንንም የዘርፉ ባለሞያዎች ሲመክሩ ኖረዋል።

የአማርኛ ቋንቋን ይበልጥ በማሳደግ ተጨማሪ ቋንቋዎችን ለፌዴራል የሥራ ቋንቋነት መጠቀም፣ በሌሎች ሀገራትም እንደታየው ሀገራዊ ጠቀሜታው የላቀ ነው። ስለሆነም አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ የፌደራል የሥራ ቋንቋዎች ቢሆኑ ልሳነ ብዙ ሀገረ መንግሥት ከመገንባትም ባሻገር ውስጣዊና ቀጣናዊ ትሥሥር ያፋጥናል። ብሎም ኅብራዊውን የብሔረ መንግሥት ግንባታ ያቀላጥፋል። የሕዝቦችንም መግባባት ያሳድጋል።

አራቱ ለተጨማሪ የፌደራል የሥራ ቋንቋነት የታጩ ቋንቋዎች፣ ማለትም አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና አፋርኛ በሀገር ውስጥ ከሽግግር ጊዜ ጀምሮ የክልል መንግሥታት የሥራ፣ የትምህርትና የአስተዳደር ቋንቋዎች በመሆን አገልግለዋል ። እነዚህን ቋንቋዎች ከማብቃትና ከማዘመን አኳያ ሊሠራ የሚገባው የቋንቋ ልማት ሥራ በአብዛኛው የተከናወነ በመሆኑ የቋንቋዎቹን ደረጃ ከክልል ወደ ፌዴራል በአንድ እርከን ከፍ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

ከምንም በላይ ደግሞ ይኽ የቋንቋ ፖሊሲ በሀገር ውስጥ በሕዝቦች መካከል ጸንቶ የቆየውን ባሕላዊና ሥነ ልቡናዊ ትሥሥር በማጎልበት ብዝኃነትን ለማክበርና ለመቀበል፤ አንድነትንም ለማጠናከር የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። የሌላን ቋንቋ መማር ወይም ማወቅ የዚያን ማኅበረሰብ ባህል፣ አሰተሳሰብ፣ ሥነ ልቡና እንዲሁም ማኅበራዊና ባህላዊ ዕሴቶችን በወጉ ለመገንዘብ ያስችላል። ማወቅ መተዋወቅ ደግሞ ፍቅርን፣ መከባበርን፣ መተሳሰብን፣ ብሎም መደመርን ያጎለብታል።

እነዚህን ቋንቋዎች የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ አድርገን በመተግበር በምናገኘው ተሞክሮ መነሻነት ሌሎች ሀገራዊ ቋንቋዎችንም ለማካተት መነሻ ዐቅም ይኖረናል። በዚህም በተናጋሪያቸው ቁጥር ከፍተኛ የሆኑ፣ የተሻለ ተደራሽነት ያላቸውና በተለያየ ደረጃ የሥራ ቋንቋ ሆነው ያገለገሉ ቋንቋዎችን ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ጥናት ይከናወናል። መሰል ቋንቋዎች ወደ የፌደራል የሥራ ቋንቋነት የሚያድጉበት አቅጣጫና የሚለሙበት ስትራቴጂም ይነደፋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.