Fana: At a Speed of Life!

በሚኒያፖሊስ ከተማ የጆርጅ ፍሎይድን በግፍ መገደል ተከትሎ ተቃውሞ በርክቷል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካዋ ሚኒያፖሊስ ከተማ የጆርጅ ፍሎይድን በነጭ ፖሊስ በግፍ መገደል ተከትሎ ተቃውሞ በርክቷል።

በከተማዋ የጥቁር አሜሪካዊውን ግድያ የሚያወግዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች አደባባይ የወጡ ሲሆን፥ ሰልፈኞቹ ፖሊስ ጣቢያ አቃጥለዋል።

ግድያውን ባወገዙበት የተቃውሞ ሰልፋቸውም “የጥቁር ህይዎት ዋጋው ስንት ነው” የሚለውንና በጥቁር አሜሪካውያን ላይ በነጭ ፖሊሶች አማካኝነት እየደረሰ ያለውን ግድያ የሚያወግዝ መፈክር አንግበዋል።

ከዚህ ባለፈም ጆርጅ ፍሎይድ ህይዎቱ ከማለፉ በፊት ያሰማውን የተማፅኖ “መተንፈስ አልቻልኩም” ቃል እና ዘረኝነትን የሚያወግዙ መፈክሮችንም ይዘው ወጥተዋል።

አሁን ላይ በከተማዋ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎም የአሜሪካ ልዩ ሃይል ወደ ከተማዋ ገብቶ ሁኔታዎችን እንዲያረጋጋ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል ተብሏል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተቃውሞ ሰበብ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆኑ አንፈቅድም ብለዋል።

ጆርጅ ፍሎይድ ባለፈው ሰኞ በፖሊሶች ከተያዘ በኋላ አንደኛው የፖሊስ አባል አንገቱን በጉልበቱ ተጭኖት በአሰቃቂ ሁኔታ ህይዎቱ አልፏል።

በወቅቱ ሟቹ ጆርጅ ፍሎይድ ፖሊሱን “እባክህን መተንፈስ አልቻልኩም፤ አትግደለኝ” እያለ ሲማጸነው የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በአካባቢው በነበሩ መንገደኞች ተቀርጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ፖሊሶች ከጆርጅ ፍሎይድ ጀርባ ላይ የነበሩ ሲሆን አንደኛው ባልደረባቸው ደግሞ ወደ መንገደኞች ፊቱን ዞሮ ሲከራከር ያሳያል።

የ46 አመቱ ጥቁር አሜሪካዊ በወቅቱ ምንም አይነት መሳሪያ አለመታጠቁ ተገልጿል።

የሟች ቤተሰቦች ፍትህን እንሻለን ቢሉም የከተማዋ ፖሊስ በበኩሉ ጉዳዩን አራት ፖሊሶችን ከስራ በማሰናበት አልፎታል።

አቃቤ ህግና የሃገሪቱ የምርመራ ቢሮ ደግሞ መረጃዎችን እያሰባሰብኩ የሚል መግለጫ ሰጥተዋል።

በአሜሪካ ነጭ ፖሊሶች በጥቁሮች ላይ የሚወስዱት ተገቢ ያልሆነ እና ያልተመጣጠነ እርምጃ እየተባባሰ መምጣቱ ይነገራል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.