Fana: At a Speed of Life!

በማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ በተደረገው የምርመራ ዘመቻ በኮቪድ19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ80 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ በተደረገው የኮቪድ-19 የምርመራ ዘመቻ ቀድሞ ከነበረው ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር በ80 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዘመቻውን የእስካሁን አፈጻጸም አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ከነሀሴ 1 እስከ ነሀሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ 182 ሺህ 497 ናሙና መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

ይህም በዘመቻው የተያዘውን 200 ሺህ ናሙና የመመርመር ግብ 92 በመቶ ያሳካ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የዘመቻው ምርመራ ከዚህ በፊት የነበረውን የመመርመር አቅም 78 በመቶ አሳድጓል ነው ያሉት።

በምርመራው ፖዘቲቭ ሆነው የሚገኙት ሰዎችም 90 በመቶዎቹ ከማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ መሆኑን ነው ያነሱት።

በዘመቻው የታቀደውን የመመርመር መጠን ከማሳካት አንጻር ውጤታማ ስራ መሰራቱንም አስረድተዋል፡፡

ከሚፈለገው አንጻር ግን በክልሎች በኩል በእኩል ያለመሄድ፣ የውጤቶች መዘግየት እና የዳሰሳው እና የምርመራ ስራዎች መዘግየት ታይቷል ብለዋል።
በሃገር አቀፍ ደረጃ በአማካይ በየቀኑ 15 ሺህ ሰዎችን በመመርመር ቀድሞ ከነበረው የምርመራ አቅም 78 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም አውስተዋል።

ከዚህ ባለፈም የግንዘቤ ማስጨበጫ ስራዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አጠቃቀም እንዲጎለብት ለመገናኛ ብዙሃን አባላት፣ ለክልል አመራሮች እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት አሳታፊ መድረኮችን በማዘጋጀት የተያዘው አቅድ እንዲሳካ ጥረት መደረጉን ጠቁመዋል።

ዘመቻው ያልተጠናቀቀ ሲሆን የቁሳቁስ እጥረት እንዳይገጥም 3 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና መሳሪያዎችና የንጽህና መጠበቂያዎች ለክልሎች እየተሰራጨ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

በትእግስት አብርሃም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.