Fana: At a Speed of Life!

በማላዊ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እንደሚደግፉ ገለፁ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  በማላዊ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በሃብታቸው እና በሙያቸው በቀጣይነት እንደሚደገፉ ገለፁ።

በናይሮቢ የኢፌዲሪ ኤምባሲ አዘጋጅነት ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ማላዊ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ቨርቹዋል የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በኬንያ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በፓናል ውይይቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ÷ ኢትዮጵያውያኑ እና  ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ካለበት ድረጃ ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ለማድረስ የማይተካ ኃላፊነት አላቸው ብለዋል።

አባይን የመገደብ ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን ራትም መብራትም ከመሆኑም በላይ ለሀገራችንና ለህዝባችን የህልውና ጉዳይ መሆኑን አምባሳደር መለስ ጠቅሰው ግድቡ እንዲጠናቀቅ በቦንድ ግዥ፣ በሙያቸውና በዜጋ አምባሳደርነታቸው የየበኩላችውን ድርሻ እንዲወጡ ወገናዊ ጥሪ አቅርበዋል።

በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ግድቡን በተመለከተ ያደረጉትን ንግግር አስመልክቶም የፕሬዚደንቱ ንግግር ኃላፊነት የጎደለው፣ የሁለቱን ሀገራት ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ጠንካራ ዲፕሎማሲ ወዳጅነት ከግምት ያላስገባ፣ ከሀቅ የራቀ እንደሆነም  አምባሳደሩ ገልፀዋል።

አባይ ላይ ግድብ ለመገንባት ኢትዮጵያ የማንንም ፈቃድ የማትጠይቅ ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን ገልፀው÷ ግንባታውን ለማካሄድ የሞራል፣ የፖለቲካ እና የህግ መብት አለን ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የማንም ሳይሆን የሁላችንም ታላቁ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ግድቡ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ መንግስት ለሚያደርገው የነቃ የመሪነት ሚና ምስጋናቸውን አቅርበው ÷ቦንድ በመግዛትና በተሰማሩባቸው ሙያ መስኮች ሁሉ የየበኩላቸውን የዜጋ አምባሳደርነት ሚና እንደዜጋም እንደባለሞያም ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በፓናል ውይይቱ በግድቡ ዙሪያ በሚደረጉ የሶስትዮሽ ድርድሮች ውስጥ በተደራዳሪነት በዲፕሎማሲው መስክ በብሄራዊ አርበኝነት እየሰሩ ያሉት አቶ ዘሪሁን አበበ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል።

የፓናል ውይይቱ ዋነኛ ዓላማ ማላዊ በሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት ዘንድ በግድቡ ዙሪያ የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖር በማስቻል በስኬት እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

የፓናል ውይይቱ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ባለሙያዎቹ መልስ በመስጠትና በግድቡ ዙሪያ የጋራ የድጋፍ ድምጽ በማሰማትና በቀጣይነት ለመደገፍ ቃል በመግባት መጠናቀቁን በናይሮቢ  የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.