Fana: At a Speed of Life!

በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካረረ የመጣው ግጭት በተለይም በአዳጊ አገራት ላይ ከፍተኛ ጫና ይኖረዋል – ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ብሩህተስፋ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካረረ የመጣው ግጭት በተለይም በአዳጊ አገራት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያስከትል የኢኮኖሚ ምሁር ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ብሩህተስፋ ገለጹ።

ጦርነት በተፈጥሮ ከሚያደርሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ውድመቱና የሚፈጥረው ጫናም ቀላል የሚባል አይደለም ብለዋል።

የጦርነት ኪሳራው ዘርፈ-ብዙ እና በርካቶችን የሚያካልል እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን÷ መቋጫ ቢያገኝ እንኳን በሰው ልጆች ዘንድ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ የከፋ ይሆናል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በዓለም ላይ የተደረጉ ጦርነቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ሁሉ መጥፎ አሻራ አሳርፈውና በርካቶችን ጎድተው አልፈዋልም ነው የተባለው።

በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካረረ የመጣው ጦርነት ብዙ መዘዞችን የሚያመጣና በርካታ ጉዳቶችን የሚያስከትል መሆኑን የኢኮኖሚ ምሁሩ ተናግረዋል።

ጦርነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚካሄድ ቢሆንም ብዙዎችን መነካካቱ እንደማይቀር ጠቅሰው÷ በተለይም በአዳጊ አገራት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጫና ቀላል አይሆንም ነው ያሉት።

በኢኮኖሚው መስክ ሩሲያ ከሳዑዲ አረቢያ በመቀጠል ሁለተኛዋ ከፍተኛ የነዳጅ ላኪ አገር በመሆኗ ጦርነቱ ሲያስተጓጉለው በሚፈጠረው የዋጋ ንረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት ተጎጂ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።

በጦርነቱ ሳቢያ በዓለም ገበያ የነዳጅ ምርት በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ እያሻቀበ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል ነው ያሉት።

በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ በተለይም በምግብ እና በነዳጅ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ልጸዋል።

ኢትዮጵያ በበጋ እያመረተችው ያለው በመስኖ የሚለማ የስንዴ ምርት ትልቅ ትርጉም አለው ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ÷ ሌሎች ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን ማብቀል ይገባል ሲሉ መክረዋል።

በግብርናው መስክ ፈጥነው የሚደርሱ የቆላ ስንዴ እና የመሳሰሉትን የምርት አይነቶች በስፋት ማልማት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

እ.ኤ.አ. በ2020 የአፍሪካ አገራት 4 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የግብርና ምርቶችን ከሩሲያ ያስገቡ ሲሆን÷ ከምርቶቹ 90 በመቶው የስንዴ ምርት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉም ተብሏል።

በተመሳሳይ ዓመት የአፍሪካ አገራት ከዩክሬን 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የግብርና ምርቶችን ሲያስገቡ 48 በመቶው የስንዴ ምርት መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.