Fana: At a Speed of Life!

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የተቋቋመው ግብረ-ሀይል ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማስቻል እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተመሰረተው የሚኒሰቴሮች ግብረ-ሀይል ስራ ጀመረ።
ግብረ-ሀይሉ ለፋና ብርካስቲንግ ኮርፖራት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግሰታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት በጋራ በተደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ላይ የተመላከቱ ምክረ-ሀሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የተጠቃለለ ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሀ-ግብር በማጽደቅ ዛሬ ስራውን በይፋ ጀምሯል።
ስትራቴጂው እና የድርጊት መርሀ-ግብር በግጭቱ ምክንያት የተፈጸሙ ሁሉንም ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚሸፍን መሆኑን ገልፆ፥ መንግስት ከወሰደው የተናጠል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም እርምጃ በኋላ በአፋር እና አማራ ክልል ተፈጸሙትንም ይመለከታል ብሏል።
ግብረ-ሀይሉ ስራውን በውጤታማነት ለማከናወን እንዲያስችለው የወንጀል ምርመራ እና ክስን፣ የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ጉዳዮችን፣ የጾታዊ ጥቃቶችን እና የሀብት ማሰባሰብን አስመልክቶ ስራዎችን የሚያስተባበሩ አራት ኮሚቴዎችን ማዋቀሩን ገልጿል።
እነዚህ ኮሚቴዎች እንደየቅደም ተከተላቸው በፍትህ ሚኒስቴር፣ በሰላም ሚኒስቴር፣ በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እና በገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚመራ ነው ያስታወቀው።
የግብረ-ሀይሉን እና የተዋቀሩትን ኮሚቴዎች የቀን ተቀን ስራዎች ለማስተባበር፣ ለመከታተል እና ለማቀናጀት ይቻል ዘንድ ራሱን የቻለ ጽ/ቤት እንዲቋቋምም ወስኗል።
ግብረ-ሀይሉ ለወንጀል ምርመራ እና ክስ ኮሚቴ የተፈጸሙ ጥሰቶችን አስመልከቶ ጠንካራ እና ግልጽነት ያለው የህግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ እንዲቻል አስፈላጊው የሞያ ነጻነት ያለው ልዩ የወታደራዊ እና መደበኛ ጥምር የወንጀል ምርመራ እና ክስ የስራ ክፍል በማቋቋም ስራ እንዲያስጀምርም አቅጣጫ አስቀምጧል።
በተጨማሪም ግብረ-ሀይሉ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ተጎጂን ማዕከል ያደረገ የአሰራር ስርዓትን እንዲከተሉ እና ትኩረታቸውም ተጎጂዎች እውነትን የማወቅ እና ፍትህ የማግኘት መብቶቻቸው አንዲከበሩ እንዲሁም አቅም በፈቀደ መጠን የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እና ካሳ የሚያገኙበትን ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንዲያተኩሩ አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቁሟል።
ግብረ-ሀይሉ ከዚህ በተጨማሪ የፍትህ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብረ-ሀይሉ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ይችል ዘንድ አግባብነት ካላቸው ሀገራዊ እና አለምአቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከአቅም ግንባታ ጋር የተያያዙ የቴክኒክ እርዳታ እና ድጋፍ እንዲገኝ ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የስራ መመሪያ መሰጠቱም ተገልጿል።
ግበረ-ሀይሉ የተጣለበትን ኃላፊነት አፈጻጸም አስመልከቶ ለህዝቡ ተከታታይነት ያላቸው ወቅታዊ መረጃዎችን የሚያቀርብ መሆኑንም አስታውቋል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.