Fana: At a Speed of Life!

በሰርጉ ላይ ላለመገኘት በሃሰት ተጠልፌያለሁ ያለው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል

አዲስ አበባ፣ ጥር 15 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሎምቢያ ፒታሊቶ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ55 ዓመት ጎልማሳ በሰርጉ ላይ ላለመገኘት የፈፀመው ተግባር ብዙዎችን አስገርሟል።

ስሙ ያልተጠቀሰው ግለሰብ ከእጮኛው ጋር ጋብቻውን ለመፈጸም እቅድ ይዞ ነበር።

ሆኖም ግለሰቡ የሰርጉ ዕለት እየተቃረበ ሲመጣ ሰርጉን ለመሰረዝ እና ከፍቅረኛው ጋር ለመለያየት ማሰቡን ለጓደኞቹ ይነግራቸዋል።

የግለሰቡን ስሜት የተረዱት ጓደኞቹም በሰርጉ ላይ እንዳይገኝ ይረዳል ያሉትን ሃሳብ ይነግሩታል፤ ለዚህም ጎልማሳው እንደተጠለፈ በማስመሰል እንዲወራ ይስማማሉ።

በዚህም የ55 ዓመቱ ጎልማሳ ራሱን እንዲደብቅ በማድረግ ጓደኞቹ ለፖሊስ ደውለው ሊያገባ ቀናት የቀሩት ጓደኛቸው በታጣቂዎች መታገቱን ይናገራሉ።

ኮሎምቢያ እገታ የተለመደባት ሀገር በመሆኗ የአካባቢው ባለስልጣናት የደረሳቸውን መረጃ ተከትሎ ጉዳዩን በትኩረት መከታተል ይጀምራሉ።

ፖሊስ እና የመከላከያ አባላትም ታግቷል የተባለውን ግለሰብ ፍለጋ ይሰማራሉ።

ለፍለጋ የተሰማራው የሰው ሃይልና እየባከነ ያለውን ሃብት የተመለከቱት የሙሽራው ጓደኞች በፈጸሙት ድርጊት ይፀፀታሉ።

ድርጊታቸው አግባብ አለመሆኑን የተገነዘቡት ጓደኞቹ ዋሽተው ጓደኛቸውን ለመርዳት መሞከራቸውን ለፖሊስ ይገልጻሉ።

የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ኔስቶር ቫርጋስም ግለሰቦቹ ሆን ብለው በማስወራት ጓደኛቸውን ለመርዳት መዋሸታቸውን አረጋግጠዋል።

ፖሊስ ሙሽራው እና ተባባሪዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፥ ሃሰተኛ መረጃን በማሰራጨት እስከ ስድስት አመት የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

ግለሰቡ ሰርጉን ለመሰረዝ ከማሰቡ ውጭ ግን ለዚህ ያበቃው ምክንያት አለተጠቀሰም።

የአካባቢው ባለስልጣናትም ግለሰቡ ከሚደርስበት ተፅዕኖ ለመከላከል ማንነቱን ከመግለፅ መቆጠባቸው ተጠቁሟል።

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.