Fana: At a Speed of Life!

በሱዳን በስደት ላይ የነበሩ 138 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሱዳን ውስጥ በስደት ለበርካታ ዓመታት የኖሩ 138 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን በሱዳን ገዳሪፍ የኢፌዴሪ የቆንስላ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ መሃሪ አንተነህ፤ ከስደት የተመለሱት ዜጎች ከ15 እስከ 30 ዓመታት በስደት የኖሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም አሜሪካ ከሚገኘው ግፉሃን ማህበር፣ ከሱዳን ፖሊስ፣ ኢሚግሬሽን፣ ጉምሩክ እና መረጃ ደህንነት መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ስደተኞቹ በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።

ሱዳን ውስጥ በተፈጠረው የኑሮ ውድነትና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በስደት ከሚኖሩባት የገዳሪፍ ግዛት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

“የምዕራብ ጎንደር ዞን አመራሮች እና የመተማ ዮሐንስ ከተማ ማህበረሰብም ከስደት ለተመለሱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠጥና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ አጋርነቱን እያሳየ ነው” ብለዋል።

የመተማ ዮሃንስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አንዳርግ ሞላ በበኩላቸው ዛሬ የመጡትን ስደተኞች ጨምሮ 338 ከስደት ተመላሾች በከተማዋ እንደሚገኙ ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ተመላሾቹ በሰጡት አስተያየት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ መንግስትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካለት የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው በሀገራቸው ሰርተው በመለወጥ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን ከመጥቀም ባሻገር በአገራዊ ኢኮኖሚ እድገቱ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ወደ ሀገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.