Fana: At a Speed of Life!

በሱዳን በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከ50 በላይ ሰዎች ሕይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን የዝናብ ወቅት ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ በጥቂቱ 52 ሰዎች መሞታቸውንና ከ8 ሺህ 170 በላይ ቤቶች መውደማቸውን የአገሪቱ  ባለስልጣናት አስታወቀዋል።

የሱዳን ባለስልጣናት እንዳስታወቁት፥ በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ የ52 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፥ 25 የሚጠጉ ሌሎች ሰዎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።

በተለይ በነሐሴ እና መስከረም ወራት የሀገሪቱ  የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የሰው ሕይወት እና የንብረት ውድመት በሚያስከትል የጎርፍ አደጋ በየዓመቱ እንደሚጠቁ ነው የአል አረቢያ ዘገባ ያስታወሰው።

የሱዳን  ብሔራዊ ሲቪል መከላከያ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ብርጋዴር አብዱልጀሊል አብዱል ራሂም እንዳሉት በሱዳን የዘነበው ኃይለኛ ዝናብ እና የተከሰተው  ጎርፍ የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

በሱዳን ሰሞኑን የተከሰተው ጎርፍ በ540 ሄክታር የእርሻ መሬት ላይም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱም ነው የተገለጸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 5 ሺህ 345 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲፈርሱ፣ 2 ሺህ 862 የሚጠጉ ቤቶች በከፊል ወድመዋል። በተጨማሪም 16 የሕዝብ መገልገያዎች፣ 39 ሱቆች እና መጋዘኖች ላይም ጉዳት ማድረሱን ኃላፊው መግለፃቸውን የግሎብ ኤኮ ዘገባ ያመላክታል።

በሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ሰኞ ትናንት እንዳስታወቀው፥ ክረምት ከገባ ጀምሮ በሱዳን 38 ሺ የሚሆኑ ሰዎች በዝናብ እና በጎርፍ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅትም 314 ሺህ 500 የሚሆኑ ሱዳናውያን  አደጋ እንዳጋጠማቸው ጽ/ቤቱ አስታውሷል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.