Fana: At a Speed of Life!

በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ለማስመለስ የተቋቋመው ፈፃሚ ብሄራዊ ኮሚቴ ባዘጋጃቸው ዕቅድ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ለማስመለስ የተቋቋመው ፈፃሚ ብሄራዊ ኮሚቴ ባዘጋጃቸው ዕቅድ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት እና በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ፀሃፊነት የተዋቀረው በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ለማስመለስ የተቋቋመው ፈፃሚ ብሄራዊ ኮሚቴ 16 መንግስታዊ ተቋማትን በአባልነት ያቀፈ ነው።

ብሄራዊ ኮሚቴው ዛሬ በካሄደው ውይይት ፥ በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ከ102 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ግብ ተቀምጦ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ፥ ኮሚቴው ዜጎችን መመለስ ብቻ ሳይሆን ድርሻ ያላቸው አካላትን በማሳተፍ መልሶ እስከ ማቋቋም የሚደርስ ስራን ለመስራት ሰፊ እንቅስቃሴን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ዜጎቻችን ያሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ጊዜ የማይሰጥ ነው ያሉት አምባሳደር ብርቱካን፥ ወገኖቻችንን ለመታደግ ሁሉም አካላት የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አያይዘውም ዜጎችን በተቻለ ፍጥነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ለውይይት የተዘጋጀውን የተግባር ዕቅድ ያቀረቡት የኮሚቴው አባል የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ መስፍን ገብረማሪያም እንዳሉት ፥ እቅዱ ዜጎቻችን የሚገኙበትን እና የሃገራችንን ወቅታዊ ሁኔታን ታሳቢ አድርጎ ተዘጋጅቷል።

የተዘጋጀው ረቂቅ እቅድ ዜጎችን ለማስመለስ ከሚሰሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አንስቶ ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም በፌደራል እና በክልል ደረጃ የሚሰሩ ስራዎችን ይዟል።
የተመላሾችን መረጃ በቅድሚያ በተሟላ መልኩ አጠናቅሮ መያዝ መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነም በውውይቱ ተጠቅሷል።

ተመላሾች ከመጡ በኋላ በመቆያ ማዕከላት መጨናነቅ እንዳይፈጠር፣ መሰረታዊ አቅርቦቶችን በሚያስፈልገው መጠን ለማቅረብ እንዲሁም አስፈላጊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል።

ለእቅዱ መተግበሪያ የሚያስፈልገው በጀት ዙሪያም ግብዓት የሆኑ ሃሳቦች መሰንዘራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሳዑዲ አረቢያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ እና በጂዳ የኢፌዴሪ ቆንስል ጄነራል አምባሳደር አብዱ ያሲን እየተደረጉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በተመለከተ ለኮሚቴው አባላት ማብራሪያ ተሰጥተዋል።

የብሄራዊ ኮሚቴው አባል መስሪያ ቤት ተወካዮች የተወያዩበት ዕቅድ በቀጣይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለሚመሩት “በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል መከላከል እና መቆጣጠር ብሄራዊ ኮሚቴ” ጸድቆ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናልም ነው የተባለው።

የኮሚቴው አባላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፍትህ ሚኒስቴር፣ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ የጤና ሚኒስቴር ፣ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የዳያስፓራ ኤጀንሲ፣ የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን፣ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሰኝ ኩነት ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ የማህበረሰበ ጤና ኢንስቲትዩት ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ፣ የኢትዮጵያ የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አገልግልት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኤርፖርቶች ድርጅት፣ የትራንስፓርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ናቸው ።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.