Fana: At a Speed of Life!

በሴቶች ጤና አገልግሎትና በስነ ተዋልዶ ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ እና ፖፑሌሽን ሰርቪስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የወደፊት ህይወታችውን ማግኘት በሚል በሴቶች ጤና አገልግሎትና በስነ ተዋልዶ ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል።
የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ የፕሮጀክቱን ይፋ መሆን በገለጹበት ወቅት÷ ባለፉት አመታት የቤተሰብ እቅድ ለማስፋፋት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገራችን ካገቡ አፍላ ወጣቶች መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት የተሟላ የቤተሰብ እቅድ እየፈለጉ አገልግሎቱንም ሆነ መረጃን ማግኘት እንዳልቻሉም ጠቁመዋል።
አያይዘውም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ከማህበራዊ አድልዎ፣ ከአስገዳጅነት እና ከጥቃት በማላቀቅ ነጻ ፍትሀዊ ትክክለኛና በእውቀት ላይ የተመሰረተ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ምርጫዎችን እንዲያገኙ በማስቻል በአፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጃገረዶች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ከግባቸው ለመድረስ እንዲችሉ ሁሉም ዕድል ሊሰጣቸውና ሊደገፋቸው ይገባልም ነው ያሉት፡፡
የማሪ ስቶፕ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ሽብሩ ፕሮጀክቱ የአፍላ ወጣቶችን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ችግሮችን የሚፈታ፣ ምላሽ ሰጪ እና ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ እድል የሚፈጥር አዲስ የጤና ፕሮግራም መሆኑንም አንስተዋል።
ወጣት ላይ መስራት ኢትዮጵያን መገንባት ነው በማለት ማሪስቶፕስ ኢትዮጵያ እና ፖፑሌሽን ሰርቪስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ለወጣቶች ትኩረት በመስጠት እየሰሩ ይገኛሉም ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከካናዳ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በጥምረት የሚተገበር ነው ተብሏል፡፡
የፕሮጀክቱ ዋነኛ ተጠቃሚዎች እድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ዓመት የሆኑ በአፍላ ወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙና ያገቡ ቢሆኑም በሁሉም የመውለድ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች፣ አጋሮቻቸውና እና ማህበረሰብ አባላት መረጃዎችንና አገልግሎቶችን የሚያገኙ ይሆናልም ነው የተባለው።
ፕሮጀክቱም በሶስት ክልሎች በ13 ዞኖችና በ39 ወረዳዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.