Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል በ2011ና 2012 የበጀት ዓመታት 53 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች በመቆፈርና በመገንባት ለክልሉ ህዝብ ተደራሽ መደረጉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት24፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በሶማሌ ክልል በ2011 እና 2012 የበጀት ዓመታት 53 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈርና በጥራት በመገንባት ለክልሉ አርብቶ – አደር ሕብረተሰብ ጥቅም እንዲውሉ መደረጉን የክልሉ የውሃ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ አዲሱ የለውጥ መንግስት ወደ ሃላፊነት ከመጣ ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ የስርዓት ሽግግር ከመዘርጋት ስራ ጎን ለጎን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ሲተገብር መቆየቱን የሶማሊ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በዚህ ለህብረተሰቡ ከተላለፉ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ባሻገር ሌሎች 15 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ ሲሆኑ በቅርብ ወራት አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሏል፡፡

ከመካከለኛ የውሃ ግድቦች ጋር በተገናኘ አምስት አዳዲስ ግድቦችን በመገንባት አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ስድስት የቆዩ ግድቦች ደግሞ ከፍተኛ እድሳት ተደርጎላቸው አገልግሎት ላይ እንደዋሉ ተጠቁሟል ፡፡

ጅግጅጋን ጨምሮ የክልሉ ትልልቅን ከተሞች የንፁህ ውሃ ችግር ለመቅረፍ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ነው የተባለው፡፡

በመሆኑም በተደረገው መጠነኛ ዳሰሳ የክልሉ የገጠር የውሃ ሽፋን ባለፉት ሁለት ዓመታት ስራ ወደ 23 በመቶ ሽፋን ሲያድግ በከተማ ደግሞ ወደ 25 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል ነው የተባለው፡፡

የክልሉ መንግስት ከሚያከናውናቸው ትልልቅ የልማት ስራዎች የውሃ አቅርቦት ሽፋን ቅድሚያ በመስጠት ከፍተኛ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.