Fana: At a Speed of Life!

በሻምፒዮናው 3ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ገባ፡፡

በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የልዑካን ቡድኑ÷ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

ለልዑካን ቡድኑ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ናቸው አቀባበል ያደረጉላቸው፡፡

ቡድኑ ነገ ከማለዳው 1 ሰዓት ከ30 ጀምሮ ከስካይ ላይት ሆቴል በመነሳት በፓትሮልና በሲቲ ቱር ባሶች ታጅቦ በአዲስ አበባ ከተማ የተመረጡ ዋና ዋና መንገዶች በመዘዋወር ዜጎችን “እንኳን ደስ አላችሁ” እንደሚሉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በዕለቱ በስካይ ላይት ሆቴል የማበረታቻ ሽልማትና የእውቅና መርሐ ግብር እንደሚካሄድም ተመላክቷል፡፡

ከሐምሌ 25 እስከ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው 19ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ6 ወርቅ፣5 የብር እና1 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አሜሪካና ጃማይካን ተከትላ ሶስተኛ ወጥታለች።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ማብቂያ ቀን በ35 ደቂቃ ውስጥ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ማምጣቷም ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.