Fana: At a Speed of Life!

በቀላል ባቡር መንገድ መሸጋገሪያዎች ላይ የሚታየውን የትራፊክ ፍሰትና የደህንነት ችግር ለመቅረፍ ያለመ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር መንገድ መሸጋገሪያዎች ላይ የሚታየውን የትራፊክ ፍሰትና የደህንነት ችግር መቅረፍ ላይ ያተኮረ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተካሂዷል።

ውይይቱን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ሰላማዊና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን እንዲሁም በቀላል ባቡር መንገድ ላይ ማሻሻያዎችን ለማካሄድ በማለም ነው ያካሄደው።

በውይይቱ ላይ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት እና ትኩረቱን በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ አድርጎ የሚሰራው ዓለም አቀፍ ተቋም ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ውይይቱ የከተማዋ ቀላል ባቡር በሚያልፍባቸው መስመሮች ላይ ህብረተሰቡ በተሽከርካሪ እና በእግር መንገዱን ለማቋረጥ አስቸጋሪ መሆኑ፣ ባቡሩ የሚያልፋባቸው መንገዶች ሙሉ በሙሉ በአጥር የተዘጉ በመሆናቸው እና ሌሎች መሰል ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙበት ላይ ያተኮረ ነው።

በኤጀንሲው እንደ መነሻ ሀሳብ የቀረበው የማሻሻያ ስራ በሰባተኛ እና አደይ አበባ አካባቢ ለሚስተዋሉ የእግረኛ እና የተሽከርካሪ ፍሰት እና ደህንነት ችግር የባቡር እንቅስቃሴውን በማያስተጓጉል መልኩ ለመተግበር የሚያስችል ነው ተብሏል።

ውይይቱ የህብረተሰቡን በተለይ በቀላል ባቡር መንገዶች እና መሸጋገሪያዎች ላይ የሚስተዋለውን የትራፊክ ፍሰት እና የደህንነት ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ ያለመ በመሆኑ እስከ ትግበራው ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልከአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.