Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዩ ሳምንት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል – የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በቀጣዩ አንድ ሳምንት ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ በመጪው አንድ ሳምንት ከክረምት ወቅት መጀመር ጋር ተያይዞ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ይኖራቸዋል ብሏል።
በተለይ በምዕራብና የደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ይጠበቃል፡፡
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ አዊ ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ኢሉአባቦራና ሁሉም የወለጋ ዞኖች ደረቅ የአየር ሁኔታ እንደሚኖራቸውን ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብና የሲዳማ ሁሉም ዞኖች፣ ደቡብ ኦሞ ኮንሶን ጨምሮ የተወሰኑ አካባቢዎች ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ ሊኖራቸው እንደሚችል ተገምቷል።
በምስራቅ ሀረርጌ፣ አርሲ፣ ባሌና ምስራቅ ባሌ እንዲሁም የተወሰኑ የጉጂ ዞኖች ደግሞ ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ሊያገኙ ይችላሉ ብሏል የኢንስቲትዩቱ መግለጫ።
ኦሞጊቤ፣ አባይ፣ ባሮአኮቦ የመካከለኛው የታችኛው ስምጥ ሸለቆ የታችኛውና መካከለኛው የተከዜ የላይኛውና የመካከለኛው ገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች እስከ ከፍተኛ እርጥበት የሚያገኙ ሲሆን÷ በጥቂት ቦታዎች ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁሟል።
በተለይ ባሮ አኮቦ የታችኛው አባይ፣ እንዲሁም ኦሞ ጊቤ ተፋሰሶች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊኖር ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አመላክቷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.