Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ኢንተርኔት በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ እንደሚሆን ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ኢንተርኔት ሙሉ ለመሉ ተደራሽ እንደሚሆን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በስሩ ከሚገኙ ተቋማት ጋር የ10 አመት መሪ እቅድና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት እያደረገ ነው።

የኢኖቬሽን ልማትና ምርምር ሚኒስትር ዘርፍ ዲኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ እንዳሉት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የምጣኔ ሃብት እድገት በዘመናዊ አሰራር መደገፍ የእቅዱ ትኩረት ነው።

ሃገራዊ ዲጂታል ምጣኔ ሃብት መገንባትና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተያዘውን ዓላማ በማሳካት የዲጂታል ምጣኔ ሃብት ዝግጁነት እንደሚጎለብትም አስታውቀዋል።

በዚህም የቴሌኮም ጥራት፣ ዋጋና ተደራሽነትን ማረጋገጥ የእቅዱ አንደኛው ግብ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ተደራሽነትን በመጭዎቹ አመታት አሁን ካለበት 18 ነጥብ 8 በመቶ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ይሆናል ብለዋል።

የሞባይል ተጠቃሚዎች ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽነትም አሁን ካለበት 37 ነጥብ 2 በመቶ በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ እውን ለማድረግ ይሰራልም ነው ያሉት።

የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ብዛትም አሁን ካለው አንድ ተቋም ወደ ሶስት ለማድረስ መታቀዱን ጠቅሰው፣ በተመሳሳይ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት መዘርጋት፣ ማጎልበትና ተደራሽ በማድረግ በኩል አሁን ካለው አንድ ብሄራዊ የዳታ ክምችት ብዛት ወደ 15 ለማድረስ መታቀዱን አውስተዋል።

ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክ ታግዘው ለህብረተሰቡ የሚደርሰው አገልግሎት ብዛት አሁን ካለበት 176 በቀጣዮቹ 10 ዓመታት 2 ሺህ 500 ይደርሳል።

በኦንላይን የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎት ድርሻ በዕቅድ ዘመኑ 85 በመቶ ለማድረስ እንደሚሰራም አንስተዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን ማስፋት ሌላኛው ግብ ሲሆን 10 አዳዲስ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ይኖራሉ የተባለ ሲሆን የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን ማስተዋወቅ 3 ሺህ 500 የንግድ ተቋማትን ወደ ኤሌክትሮኒክ ግብይት እንደሚገቡ አስረድተዋል።

የእውቀትና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተደራሽ ከማድረግ አንጻርም በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺህ በላይ የለሙ የዲጂታል ዕውቀት ይዘቶች የሚገኙ ሲሆን፤ በ10 ዓመታት ውስጥ ከ14 ሺህ በላይ እንደሚያድግም ጠቅሰዋል።

እቅዱን ለማስፈጸም ከ4 ሺህ 200 በላይ የሰው ሃይልና ከ157 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል መባሉን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.