Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪውን ሸኔ ለማጥፋት የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ውጤታማ እየሆነ ነው – ብ/ጄ ከበደ ገላው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብና የመንግስት ተቀናጅቶ መስራት አሸባሪውን ሸኔ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ እያደረገው ነው ሲሉ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ወለጋ ዞን ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ከበደ ገላው ገለጹ።

ጀኔራል መኮንኑ እንደገለጹት÷ በተለይ ባለፈው አንድ ወር ፀጸጥታ ኃይሉና በህብረተሰቡ የተቀናጀ ጥረት ከየምዕራብ ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በአሸባሪው ቡድን የተዘረፉ የህብረተሰቡ ንብረቶች እየተመለሱ ነው፡፡

በዞኑ በግምቢ ወረዳ ሶጌ ከተባለው አካባቢ፣ በቦጂ ጨቆርሳና ግምቢ አካባቢዎች ተዘርፈው የነበሩ 105 የቀንድ ከብቶችና 10 በጎች እንዲሁም ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ በቆሎ ለየባለቤቶቹ እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም 10 ሞተር ብስክለት፣ 200 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ 108 የዲሽቃ ጥይቶች፣ ድምጽ አልባ የጦር መሳሪያዎችና አንድ ጀኔሬተር ከአሸባሪው ቡድን መያዛቸውን አብራርተዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅቱ ያለምንም ስጋት በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የየዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊት በቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚያበረታታ መሆኑንም የዞኑ ነዋሪዎች ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ በተወሰደው ጠንካራ እርምጃ፥ በርካታ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ሲደመሰሱ አመራሮቻቸውን ጨምሮ አምስት ታጣቂዎች መማረካቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

እንዲሁም የሽብር ቡድኑ ለጥፋት ይጠቀምባቸው የነበሩ 5 ሙሉ ትጥቅ፣ 310 የክላሽ ጥይት፣ 2 የጭስ ቦንብ፣ 15 የጥይት መጋዘን እና የተለያዩ ወታደራዊ ንብረቶች መማረካቸው ተገልጿል።

የአሰሳ ዘመቻው ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.