Fana: At a Speed of Life!

በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ሌሎች ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ተገለፀ።

የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለቀለት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ማምረት ስራ ከተሰማሩ የውጭ ባለሃብቶች ጋር ተወያይቷል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአግሮ ፕሮሠሲንግ እና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተካ ገብረእየሱስ በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ከሰሞኑ በከፊል የተዘጋጁ ቆዳዎች ላይ ተጥሎ የነበረው 50 በመቶ ግብር እንዲነሳ የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

የመመሪያው አላማ የሃገር ውስጥ ባለሃብቱን ከውጭ ሃገር ባለሃብቶች ጋር በማስተሳሰር ሁሉንም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችን እኩል ተጠቃሚ ለማድረግና ሃገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ባለቀለት ቆዳ ማምረት የተሰማሩ የውጭ ባለሃብቶች በመመሪያው መተግበር ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ አስረድተዋል።

የውጭ ባለሃብቶች በበኩላቸው የመመሪያውን መዘጋጀት ተከትሎ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰትና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ሊሰራ ይገባል ማለታቸውን ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.