Fana: At a Speed of Life!

በበርሃ አንበጣ መንጋ ሰብላቸው የወደመባቸው አርሶ አደሮች በሴፍቲኔት እንዲታቀፉ በማድረግ የእለት ምግብ ፍጆታ ሊቀርብላቸው ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በበርሃ አንበጣ መንጋ ሰብላቸው ሙሉ ለሙሉ የወደመባቸው አርሶ አደሮች በሴፍቲኔት እንዲታቀፉ በማድረግ የእለት ፍጆታ ምግብ ሊቀርብላቸው መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ድጋፍ የሚደረግላቸው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ቀርቦላቸው በመስኖ እና በዝናብ በፍጥነት የሚደርሱ ሰብሎችን ማልማት ለማይችሉ አርሶ አደሮች ነው ብለዋል።

ይህን ተግባራዊ ለማድረግም የባለሙያዎች ቡድን ጉዳት ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች ተሰማርቶ መረጃ እያሰባሰብ ይገኛል ነው ያሉት።

በመስኖ ማልማት ለሚችሉ እና የአጭር ጊዜ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች ግን የአጭር ጊዜ የምግብ እርዳታ እየቀረበላቸው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ መንግስት እንዲያቀርብ በማድረግ ዳግም እንዲያለሙ ይደረጋልም ተብሏል፡፡

የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር አምስት የኬሜካል መርጫ እና የቅኝት አውሮፕላኖች በስራ ላይ ናቸው ያሉት ዶክተር ማንደፍሮ በትናንትናው ዕለት ተጨማሪ አንድ አውሮፕላን የመገጣጠሙ ስራ አልቆለት ወደ መከላከሉ ስራ መግባቱን አንስተዋል።

የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ዛሬ ተጨማሪ አንድ አውሮፕላን ወደ ስራ የገባ ሲሆን እስከ መጭው አርብ ድረስም ሁለት አውሮፕላኖች ወደ ስራ ይገባሉም ነው የተባለው፡፡

በአጠቃላይም በስምንት አውሮፕላኖች የአንበጣ መንጋውን የመከላከል ስራ ይከናወናልም ብለዋል ሚኒስትር ዲኤታው።

የአንበጣ መንጋው ከአርሶ አደሮች የሰብል ምርት ጉዳት አልፎ ሃገራዊ ምርትን እንዳይቀንስ በተያዘው ዓመት 600 ሺህ ኩንታል ስንዴ በቆላማ አካባቢዎች ለማልማት እቅድ መያዙንም አስረድተዋል።

አሁን ላይ የበርሃ አንበጣ መንጋው አድማሱን እያሰፋ አምስት ክልሎችን እና አንድ የከተማ አስተዳደር ማዳረሱንም ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ የአንበጣ መንጋው በሃገሪቱ የግብርና ዘርፍ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከልም የምርምር አቅምን ማሳደግ፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም እና የአውሮፕላን ግዥ መፈፀም በእቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡

በበላይ ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.