Fana: At a Speed of Life!

በበዓላት የመሠረታዊ ፍጆታ አቅርቦትና ስርጭት ላይ በልዩ ትኩረት ይሰራል – ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲሱ ዓመት የሕዝብ በዓላት ወቅት የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች አቅርቦትና ስርጭትን ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ከክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በበዓላት ወቅት የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች አቅርቦትና ስርጭት አፈጻጸም በሚሻሻልበት ጉዳይ ላይ ተወያይቷል፡፡

ውይይቱ ባለፉት ወራት የነበረውን የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች አቅርቦትና ሥርጭት አፈጻጸም በመገምገም የታዩትን ጥንካሬዎች ለማስቀጠልና የነበሩትን ክፍተቶች ለማረም ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በበዓላት ወቅት የመሰረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች ሥርጭት ላይ እጥረት እንዳይኖር አመራሩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የንቅናቄ ሥራ በመስራት ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን መስራት እንደሚጠበቅበት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ተናግረዋል፡፡

በተለይም አቅም ያላቸው አቅራቢዎችን እና የሕብረት ሥራ ማኅበራትን በማሳተፍ እንዲሁም የከተማ ግብርና የምርት ውጤቶችን በማካተት የዘይት፣ የስኳር፣ የሽንኩርት፣ የእንቁላል፣ የጤፍ፣ የቂቤ ምርቶች አቅርቦት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተጠቁሟል።

የቁም እንስሳት አቅርቦት በወቅቱና በበቂ መጠን ለገበያ የሚቀርብበትንና ሕብረተሰቡም በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሸምት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲሰሩ መግባባት ላይ ተደርሷልም ነው የተባለው፡፡

የንግድ ሥርዓቱንም ለማዘመን በሁሉም ክልሎች የተጀመረው የሪፎርም መርሐ ግብር ትግበራ አፈጻጸም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል መባሉን ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.