Fana: At a Speed of Life!

በቡርጂ ልዩ ወረዳ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ከኦሮሚያ ክልል ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 27፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ በሀገራዊና ክልላዊ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከቡርጂ ልዩ ወረዳ የህዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
 
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በቡርጂ ልዩ ወረዳ ግንባታው ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ የቀረውን የቡርጂ ሆስፒታልን በመጎብኘት ነው ከልዩ ወረዳው የህዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት ያካሄዱት፡፡
 
በውይይት መድረኩ ተሳታፊ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት የቡርጂ ህዝብ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የሆነ ስጋት ውስጥ ሆኖ ነው ኑሮውን እየገፋ ያለው ብለዋል፡፡
 
በተለይ በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በታጣቂዎች አማካኝነት የአካባቢው ነዋሪዎች በመንገድ ላይ እና በእርሻ ስፍራዎች የግድያ እና ዘረፋ የወንጀል ተግባራት እየተፈጸመብን ነው ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
 
ከምንም በላይ አሳሳቢ የሆነው የአካባቢው የጸጥታ ጉዳይ ላይ መንግስት በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡
 
ነዋሪዎቹ ልዩ ወረዳው ወደ ዞን እንዲያድግ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበን ምላሽ አላገኘንም ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
 
በየጊዜው እየተከሰተ ያለውን የጸጥታ ችግር ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመነጋገር ዘላቂ ሰላም ማስፈን ይገባል ብለዋል፡፡
 
ዩኒቨርሲቲ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኝ መንገድ ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት እና ሌሎች መሠል የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እንዲመለስላቸው ጠይቀዋል፡፡
 
በልዩ ወረዳው ግንባታው ለረጅም ጊዜ እየተጓተተ የሚገኘው ሆስታል ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡
 
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ከነዋሪዎቹ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ የደቡብን እና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ህዝቦችን እርስ በርስ በማጋጨት እና ቀጠናውን በመረበሽ የራሳቸውን ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ ሀይሎች እንዳሉ ተገንዝበናል ብለዋል ፡፡
 
በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመነጋገር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ይሰራልም ሲሉ ነው የጠቆሙት፡፡
 
የአደረጃጃት ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ መንግስት ከህብረተሠቡ ጋር በመምከር ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል በማለት ማብራራታቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ ማጤን ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በቂ የምክክር ጊዜ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
 
ተጀምሮ ያልተጠናቀቀውን የሆስፒታል እና የገበያ ማዕከል ግንባታ ስራም በሚቀጥሉት ወራቶች ለማስቀጠል ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
 
የንጹህ መጠጥ ውሀ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.