Fana: At a Speed of Life!

በባህር ዳር ከተማ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ድልድይ ፕሮጀክት ስራ እየተፋጠነ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በሆነ ወጪ በባህር ዳር ከተማ እየተገነባ ያለው አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ የግንባታ ፕሮጀክት ስራ እየተፋጠነ ነው።

በቻይናው ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ እየተገነባ ያለው ድልድይ ግንባታ ከተጀመረ ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን የግንባታ አፈጻጸሙ በእቅዱ መሰረት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል።

አሁን ላይ በዋነኝነት ከመሬት በታች የድልድዩ የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶች ቁፋሮ እና አርማታ ሙሌት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ያስታወቀው።

380 ሜትር ርዝመትና 43 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ድልድይ የግንባታ ስራ በአጠቃላይ ድልድዩን ለመሸከም ከሚያስፈልጉ 88 የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶች ውስጥ 48 የሚሆኑት የቁፋሮ እና የአርማታ ሙሌት ስራ ማከናወን መቻሉም ተገልጿል።

ድልድዩ በግራና በቀኝ በአንድ ጊዜ 6 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ እየተገነባ ሲሆን፥ የብስክሌት ተጠቃሚዎች መስመር እና 5 ሜትር የእግረኛ መንገድም ያካተተ ነው ተብሏል።

ለድልድዩ ግንባታ የቱርኩ ቦቴክ እና የሃገር ውስጥ አማካሪው እስታዲያ በተቆጣጣሪነት እና በአማካሪነት እያገለገሉ ሲሆን፥ የድልድዩ የግንባታ አይነት በተሻሻለ መንገድ በገመድ የተወጠረ ዲዛይን ያለው መሆኑንም ባለስልጣኑ ገልጿል።

አዲሱ ድልድይ ነባሩ ድልድይ ከተገነባ 60 አመታትን በማስቆጠሩና በአገልግሎት ብዛት ለተደጋጋሚ ጉዳት በመዳረጉ ምክንያት ነው የሚገነባው።

የድልድዩ ግንባታ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ አጠቃላይ ወጪውም በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.