Fana: At a Speed of Life!

በቤንሻንጉል ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ላይ የክልሉ ፓሊስ አባላት በቦርዱ ግቢ ውስጥ ያደረጉት የእስር ሙከራ ተገቢነት የሌለው ነው- ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤንሻንጉል ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ላይ የክልሉ ፓሊስ አባላት በምርጫ ቦርድ ዋና መስሪያ ቤት የእስር ሙከራ ማድረጋቸው ተገቢነት የሌለው መሆኑን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

መጪው ምርጫ የሚካሄድበትን አውድ ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት የሚመለከታቸው አካላት ሊያግዙት እንደሚገባ ቦርድ ገልጿል።

ለመጪው ምርጫ ዝግጅት በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚነሱ አቤቱታዎችን በማሰባሰብ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት ሲደርግ እንደነበር ይታወቃል።

የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለአቤቱታዎቹ ምላሽ እንዲሰጡ ማድረግ፣ ምላሽ ላልተሰጠባቸው አቤቱታዎች የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት ጥረቶች ተደርገዋል ነው ያለው።

በቅርቡ በፓርቲዎች እና ከመንግስት ጋር በተደረገው ውይይት ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በማጠናቀር ያቀረበ ሲሆን ይህንን መሰረት አድርጎ ፓርቲዎች፣ ገዥው ፓርቲ እና ቦርዱ በጋራ በመገኘት ችግሮችን የሚፈቱበት የሶስትዮሽ ችግሮችን እና አቤቱታዎችን የሚፈታ አሰራር እንዲቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን ያስታወሰው።

በዚህም መሰረት የመጀመሪያው የሶስትዮሽ ውይይት በትላንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቢሮ የተከናወነ ሲሆን በቤኒሻንጉል ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ እንዲሁም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገኝተዋል ነው የተባለው።

በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የመንቀሳቀስ የአባላት እስር እና ሌሎች ችግሮች የተነሱ ሲሆን÷በገዥው ፓርቲ በኩል የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ሆነው በወንጀል እና በትጥቅ ትግል መሳተፍ ችግሮች አሉ የሚል አቤቱታ ቀርቧል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያም በክልሉ ውስጥ ያለውን የፓርቲዎች ችግር ለመፍታት ቦርዱን ጨምሮ ሁሉም አካላት የሚሳተፉበት ቡድን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመሄድ ለማጣራት ስምምነት ተደርጎ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

ነገር ግን ውይይቱ ተጠናቆ በቤንሻንጉል ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት የምርጫ ቦርድ ዋና መስሪያ ቤት ጊቢን ለቅቀው ለመውጣት ሲሞክሩ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፓሊስ አባላት የእስር ሙከራ አድርገውባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህ ገንቢ እና ችግሮችን ለመፍታት ተስፋ ሰጪ አቅጣጫ ከነበረው በተቃራኒ በተከናወነው እርምጃ ከፍተኛ ቅሬታ ተሰምቶታል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፓሊስ ከህጋዊ የስልጣን ወሰኑ ውጪ ያለምንም የፍርድ ቤት ትእዛዝ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ በር ላይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላትን ለማሰር መሞከሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የሚያሰናክል እና አሳሳቢም ከመሆኑም በላይ የህገመንግስታዊውን የቦርዱን ተቋማዊ ሃላፊነት እና ስልጣን ንቀትን ማሳየት ጭምር ነው፡፡

ቦርዱ ችግሩን ለመፍታት ከሰአታት ጥረት በማድረግ ከአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን እና ከፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን በተገኘ እገዛ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፓሊስ ሃይል ከምርጫ ቦርዱ ዋና መስሪያ ቤት በር ላይ ከ3 ሰአት ቆይታ በኋላ አንዲነሳ ለማድረግ ቢቻልም የተከናወነው የህግ ጥሰት እና ተቋማዊ ስልጣንን አለማክበር እጅግ አሳሳቢ ነው ብሏል ቦርዱ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ቀጣዩ ምርጫን ተከትሎ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግስት በመዋቅሮቹ የስነስርአት ደንብ አክብረው እንደሚንቀሳቀሱ በይፋ ያረጋገጡትን የሚቃረን በመሆኑ መስተካከል የሚገባው መሆኑን እንደሚያምንም ገልጿል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው አቤቱታዎች ላይ የሚደረገው የሶስትዮሽ ችግሮችን መፍታት ሂደት የሚቀጥል ሲሆን መጪው ሀገራዊ ምርጫ አለም አቀፍ ተቀባይነት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በዚህ ሂደት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ቦርዱ በአጽንኦት አሳስቧል፡፡

 

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.