Fana: At a Speed of Life!

በብሪታኒያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ዜጎች በቤታቸው እንዲቆዩ ተወስኗል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሪታኒያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት 66 ሚሊየን የሚጠጉ የሀገሪቱ ህዝቦች በመኖሪያ ቤታቸው እንዲቆዩ ውሳኔ ተላልፏል።

በአሁኑ ወቅት በብሪታኒያ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 335 መድረሱን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከ7 ሺህ በላይ መድረሱ ነው የተገለጸው።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ፥ ዜጎች  በጣም አስፈላጊ የሆኑ  ስራዎችን ለማከናወን ካልሆነ በስተቀር ከቤት ውጭ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

በዚህ መሰረትም ዜጎች አስፈላጊ ሸቀጦችን ለመግዛት፣ ህሙማንን ለመርዳት፣ የተናጠል ስፓርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እና  መድሃኒት ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ከቤት ውጪ መንቀሳቀስ አይችሉም።

ከዚህ ባለፈም ዜጎች ከጓደኞቻቸው ብሎም  ከቤተሰብ አባል ውጪ ከሆነ ሰው ጋር  ባለመገናኘት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ስራ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ውሳኔው ለሶስት ሳምንታት የሚጸና መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥እንደ ሁኔታው ሊሻሻል እንደሚችልም ጠቁመዋል።

እገዳውን በመተላለፍ ከቤት ውጭ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ቅጣት እንደሚጠብቀውም አስጠንቅቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ህይታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 16 ሺህ 574 መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 382 ሺህ 108 ከፍ ሲል፤ 101 ሺህ 857 የሚሆኑት ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል።

ምንጭ፥አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.