Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሱዳን ለግብጽ እንደወገነች ተደርጎ የሚሰራጨው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው – በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ሱዳን ለግብጽ ወግናለች በሚል በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚሰራጨውን ወሬ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር አብደል ቢላል አብደልሰላም አጣጣሉ።
 
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጅማሮ አንስቶ ላለፉት ስምንት ዓመታት አያሌ ምክክሮችን ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
 
ሆኖም ካለስምምነት የተቋጨው የሶስትዮሽ ድርድሩ በመጨረሻ ወደ በዋሽንግተን በአሜሪካና ዓለም ባንክ ታዛቢነት ሲካሄድ ቆይቷል።
 
በአሜሪካና ዓለም ባንክ ታዛቢነት ለሳምንታት የዘለቀው ድርድሩ፤ በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ ያልተቋጩ ጉዳዮች እንዳሏት በመግለጽ መድረኩን እንደማትታደም አሳውቃ ነበር።
 
ይህን ተከትሎም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሱዳን ለግብጽ እንደወገነች ተደርጎ እየተስተጋባ ይገኛል።
 
በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር አብደል ቢላል አብደልሰላም ÷ የሚሰራጨው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው ብለዋል።
 
የዚህ መሰረተ ቢስ መረጃ ምንጮችም መቀመጫቸውን ግብጽ ካደረጉ የማህበራዊና መደበኛ መገናኛ ብዙሃን የሚመነጭ እንደሆነ ገልጸዋል።
 
ሱዳን ባላት እውነተኛ ፍላጎት ለግድቡ ያልተቆጠበ ድጋፍ በማድረግ ከኢትዮጵያም ጋር በትብብር መስራቷን አስታውሰው፤ የሱዳን ድጋፍ ባይታከልበት ኖሮ ፕሮጀክቱ እዚህ አይደርስም ብለዋል።
 
ሱዳን ከቴክኒካል የውሃ ግድብ አሞላል ጉዳዮች ይልቅ በአባይ ወንዝ ዙሪያ የጋራ ትብብር ሁልጊዜም አስፈላጊ መሆኑን እንደምታምን ገልጸው፤ ሀገራቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በውሃ መጠን ላይ ጉዳት የለውም የሚል እምነት መያዟን ተናግረዋል።
 
አምባሳደሩ አያይዘውም ጥቃቅን ልዩነቶች ይፈታሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸውና ሀገሮቹ በጉዳዩ ላይ ረጅም ርቀት የተጓዙ በመሆኑ ያን ያህል ተጽዕኖ ያሳድራሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ነው የገለጹት።
 
“በህዳሴው ግድብ ላይ በተደረጉ ድርድሮች የተለያዩ ከበድ ያሉ ጉዳዮች በመታለፋቸው ቀሪ ጉዳዮች ከዚህ ግባ የማይባሉ ናቸው” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.