Fana: At a Speed of Life!

በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና የማግኘት ጥያቄ መብታችንን የማስከበር ጉዳይ ነው – ዩዌሪ ሙሴቬኒ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንዲኖራት የማድረግ እንቅስቃሴ ወረታ ሳይሆን መብታችንን የማስከበር ጉዳይ ነው ሲሉ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ተናገሩ።

አፍሪካን በመወከል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያዎችን አስመልክቶ ድርድር እያደረጉ የሚገኙ የ10 የአፍሪካ ሀገራት ኮሚቴ (ኮሚቴ-10) ተወካዮች የደረሱበትን ሂደት በሚመለከት ትናንት በኡጋንዳ ካምፓላ ውይይት አድርገዋል።

የ10 የአፍሪካ አገራት ኮሚቴ ኬንያ፣ ኢኮቶሪያል ጊኒ፣ ናምቢያ፣ ዛምቢያ፣ ሊቢያ፣ አልጄሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ሴኔጋል፣ ኡጋንዳና ኮንጎ ሪፐብሊክን የያዘ ነው።

ኮሚቴው አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ሁለት ቋሚ መቀመጫና በምክር ቤቱ ቋሚ ባልሆኑ ውክልናዎች ሁለት ተጨማሪ የአፍሪካ አገራትን መጨመር አላማው አድርጎ እየሠራ ይገኛል።

የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሁን ያለበት ቁመና ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ የነበረውን ጊዜ እንጂ የዓለምን አሁናዊ ሁኔታ የሚወክል አይደለም ማለታቸውን የቻይናው የዜና ወኪል ዥንዋ ዘግቧል።

አፍሪካ ጥቅሞቿንና ፍላጎቷን ለማስጠበቅ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንደሚያስፈልጋትና ቋሚ ውክልና ማግኘቷ ምክር ቤቱ አሉታዊ ጉዳት በአህጉሪቱ ላይ እንዳያደርስ ያደርጋል ብለዋል።

1 ነጥብ 3 ቢሊየን ሕዝብ ያላት አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ማግኘት እንደሚገባት ነው በድጋሜ የገለጹት ።

ዓለም አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና የማግኘት ጥያቄዋን፥ መብትን የማስከበር ጉዳይ እንጂ ወረታ እንደመጠየቅ አድርጎ ሊያየው እንደማይገባም ነው ሙሴቬኒ ያስገነዘቡት።

የሴራሊዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ጆን ፍራንሲስ በበኩላቸው ÷ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ውይይት የሚያደረግባቸው ጉዳዮች 70 በመቶ አፍሪካ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ቢሆንም አፍሪካ ግን በምክር ቤቱ እስካሁን ቋሚ መቀመጫ የላትም ብለው ኢ-ፍትሃዊነቱ ፍጹም መቀጠል እንደሌለበትም ነው ያሳሰቡት።

አፍሪካውያንም ችግሮች ሳይበግሯቸው በጋራ እና በጽናት በመቆም ትግሉን ከዳር ማድረስ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶዬ በበኩላቸው÷ የአፍሪካ ሕብረት በእውተኛ ትብብርና በባለብዙ መድረኮች የዲፕሎማሲ ግንኙነት መርህ እንደሚያምን ተናግረዋል።

አፍሪካ ረዥም ጊዜ ሊጠይቅ በሚችለው የተመድ ተቋማዊ የማሻሻያ ሂደት እጇን ሳትሰጥ የጀመረችውን ጉዞ መቀጠል አለባት ማለታቸውን ኢዜአ ሽንዋን ጠቅሶ አመላክቷል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.