Fana: At a Speed of Life!

በታለመለት የነዳጅ ድጎማ አተገባበር ቅድመ ዝግጅት ላይ ግምገማ ተካሄደ

አዲ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከታለመለት የነዳጅ ድጎማ ፕሮግራም አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በትግበራው ዝግጅት ዙሪያ ግምገማ ተካሄደ፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ከታለመለት የነዳጅ ድጎማ ፕሮግራም አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በቅድመ ትግበራው ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ግምገማ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የታለመለት የነዳጅ ድጎማውን በተያዘለት ጊዜ ለማስጀመር የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን በግምገማው መታየቱንም ነው የገለጹት፡፡
የታለመለት የነዳጅ ድጎማውን በሁሉም ሀገሪቱ ክፍል ክፍል ለመተግበር የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር መዘጋጀቱን አስታውሰው÷ የድጎማው ተጠቃሚ የሚሆኑ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች መረጃ የማደራጀት ስራው በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
የታለመለት የነዳጅ ድጎማን ሥርዓት በማስተግበርና መሪ ሚናውን በመጫወት ረገድ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ኃላፊነት ተረክቦ ከተለያዩ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል፡፡
ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ለሚደረገው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሀገራችን ሲተገበር የቆየውን ጥቅል የነዳጅ ድጎማ ስርዓትን በማስቀረት÷ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ብቻ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት በመዘርጋት ለተወሰነ ጊዜ የታለመ የነዳጅ ድጎማ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.