Fana: At a Speed of Life!

በታሪክ ላይ ተገቢውን እሳቤ መያዝ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ጉልህ ፋይዳ አለው -የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በታሪክ ላይ ትክክለኛውን ነገር መያዝ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት “የሰላም ወግ፤ ብሔራዊ መግባባት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር “የሰላም ወግ” በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄዱ ካሉ መድረኮች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

መድረኩ አገራዊ መግባባት ለማምጣትና የተዛቡ አስተሳሰቦችን በትክክለኛው ቦታ ለማስቀመጥ ሁሉም የሚሳተፍበትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውይይት እንደሚደረግበት ገልጸዋል።

በታሪክ ላይ ተገቢውን እሳቤ መያዝ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ጉልህ ፋይዳ አለው ያሉት ሚኒስትሯ፤ “በእውቀት ላይ ተመስርተን ለእውነት የተጠጉ ሃሳቦችን ለመያዝ ተቀራርቦ መወያየትና መነጋገር ተገቢ ነው” ብለዋል።

መድረኩ ከግል ስሜትና ከቡድን ፍላጎት በፀዳ መልኩ ለጋራ ሀገር ግንባታ ጥቅም ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓለ ፈለገ ሰላም ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌውን ጨምሮ የመቐሌ ዩኒቨርሲቲ የቅርስ ጥናት ትምህርት መምህር ዶክተር አየለ በከሪና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ የውይይት መነሻ ፅሁፍ አቅርበዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ጽሁፋቸው ለብሔራዊ መግባባትና አገር ግንባታ ታሪክ ጉልህ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ህብረ ብሄራዊ አገሮች ታሪክ በትክክለኛው መንገድ ከተነገረና ተሰንዶ ከተቀመጠ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስር ይፈጥራልም ብለዋል።

እያንዳንዱ አገር ታሪኩን እያስጠና የሚያስቀምጠው ትውልድን መገንቢያ ሀብት በመሆኑ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዶክተር አልማው የአገሪቱ ታሪክ በትክክለኛው መንገድ ተፅፎና ተሰንዶ ባለመቀመጡ ታሪክን በተገቢው ሁኔታ እንዳንረዳ አድርጎናል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ታሪክ በብዛት የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት በመጡ የውጭ ተጓዦችና ሚሽነሪዎች በመጻፉ ግጭቶች በየቦታው እንዲቀሰቀሱ መነሻ መሆኑንም አብራርተዋል።

ሆኖም ታሪክ ትምህርት ቤት እንጂ፤ የግጭት መንስኤ አለመሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።

ዶክተር አየለ በበኩላቸው “የሰው ልጅን በተዛባ ታሪክና በተፈበረከ ጥላቻ እምቅ ሀይሉን ተግባር ላይ ሳያውል በድንገትና በጭፍን መቅጠፍ የከፋ ወንጀል ነው” ብለዋል።

ልዩነቶችን በመግባባትና በውይይት ለመፍታት መሞከርና ለሰው ልጅ የሚገባውን ክብር መስጠት እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.