Fana: At a Speed of Life!

በትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ትምህርት ለመጀመር ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው – ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር ለ7 ወራት የተቋረጠውን መደበኛ ትምህርት ለማስቀጠል በትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ትምህርት ለመጀመር ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ መንግስት በትምህርት ቤቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፣ የውሃ እና የእጅ ማፅጃ አቅርቦቶችን በማሟላት እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን የማፅዳት ስራዎችን በማከናወን መደበኛ ትምህርት እንደሚጀመር ነው የገለጸው፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ተማሪዎች እንደየደረጃው ወደ ክፍል ገብተው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ሲጀመርም በአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚጀመር ሲሆን በቀጣይም ሌሎች የትምህርት ክፍሎች ወደ መደበኛ ትምህርቱ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀመጡ ጥንቃቄዎች ሙሉ በሙሉ የሚተገበሩ መሆኑን እና የትምህርት አሰጣጡ ሂደትም በፈረቃ የሚሰጥ መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

የፈረቃ ስርዕቱም እንደየአካባቢው ሁኔታ ከ2 እስከ 3 ሊሆን እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በትምህርት ቤት ውስጥ መምህራኖች ትልቁን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

መደበኛ ትምህረቱም መንግስት ውሳኔ እንዳሳለፈ እንደሚጀምር መነገሩን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንደሚቻል ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.