Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ለችግኝ ተከላ የሚውል 25 ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መሳሪያ ተለይቷል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ በዘንድሮው ክረምት ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ የሚውል 25 ሺህ ሔክታር መሬት በዘመናዊ መሳሪያ የመለየት ስራን ጨምሮ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የደን ልማት አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ሙዑዝ ሃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት እስከ አሁን ለተከላ አገልግሎት የሚሆን 25 ሺህ ሄክታር መሬት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በዘመናዊ መሳሪያ /ጂፒኤስ/ የመለየት ስራ ተከናውኗል ።

ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ እርጥበትን ለማከማቸት የሚያግዙ ስራዎችን ሲከናወኑ መቆየታቸውንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የችግኝ ልማት ስራው ለማሳካት የ13 ሚሊዮን ጉድጓዶች ቁፋሮ መጠናቀቁን አቶ ሙዑዝ ገልፀዋል።

በድህረ ተከላ ወቅት ለሚደረገው እንክብካቤ የሚያግዙ የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶች የመቆፈር ስራም በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ይገኛል ተብሏል ።

እስከ አአሁን  ድረስም ከ100 ሺህ እስከ 600 ሺህ ሊትር የውሃ መጠን የመያዝ አቅም ያላቸው 62 የውሃ ማጠራቀሚያ አነስተኛ ኩሬዎችን እንዲቆፈሩ ተደርጓል ።

የተከላ ቦታዎች ለምነትን ለማጎልበት የሚጠቅም የተፈጥሮ ፍግ ወደ ተከላ ቦታዎች የማጓጓዝ  ስራ እየተከናወነ መሆኑን ዳይሬክተሩ አያይዘው ገልፀዋል ።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን የእንዳመኾኒ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሕሉፍ በላይ በሰጡት አስተያየት ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ እስከ አሁን 50 የሚሆኑ ጉድጓዶችን ቆፍረው ለተከላ ዝግጁ አድርገዋል ።

አርሶ አደሩ እንዳሉት በአካባቢያቸው ያለው የችፕውድ ፋብሪካ የገበያ ፍላጎት በመገንዘብ የባህርዛፍ ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅተዋል ።

ከአካባቢያቸው ማህበረሰብ ጋር በመሆኑን ሁለት የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችን መቆፈራቸው የተናገሩት ደግሞ በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ የባርካ ዓዲሰብሓ ነዋሪ አርሶ አደር ሃይለስላሴ ተስፋይ ናቸው።

የውሃ ማጠራቀሚያዎቹ በክረምት ወቅት የሚጥለውን ዝናብ በማቆር በበጋ ወቅት ችግኞቹን ለማጠጣት የሚያግዝ መሆኑን ህዝቡ እንዲረዳው በመደረጉ በነፃ ጉልበት ኩሬው እንዲዘጋጅ አድርገናል ብለዋል ።

በክልሉ ዘንድሮ 80 ሚሊዮን የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን ከሰኔ 15  2012 ዓ.ም ጀምሮ የተከላ ስራውን ለማከናወን  መታቀዱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.