Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለማጠናከር የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ከህግ ማስከበር እንቅስቃሴው ጋር ተያይዞ ችግር ላጋጠማቸው ወገኖች እየቀረበ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማጠናከር የሚያስችል መመረያ ተግባራዊ መደረጉን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ።
በክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት በተዘጋጀው የኬላ የፍተሻ ስርዓት መመሪያና አተገባበሩ ዙሪያ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይና የፀጥታ አካላት በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የረድኤት ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ እንደተናገሩት መመሪያው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ባከበረ መልኩ የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታና ሌሎች ድጋፎችን ለማቀላጠፍ እንዲያስችል የተዘጋጀ ነው።
በክልሉ የሚገኘው የጸጥታ ምክር ቤት አስፈላጊውን ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ዘዴ በመጠቀምም በክልሉ የሚደረገው የድጋፍ አሰጣጥ እንቅስቃሴ የዜጎችን ደህንነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግ አመልክተዋል።
በዚሁ ወቅት ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ችግሮችም የፈጣን ጥሪ ማእከል መዘጋጀቱን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው ይሄም ጠያቂዎቹ ባሉበት ሆነው ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
መመሪያው ቀደም ሲል ከመንግስትና ከሌሎች የረድኤት ድርጅቶች ለተጎጂዎች የሚቀርቡ ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማጓጓዝ የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚያቃልል እንደሆነም ተናግረዋል።
የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲባል በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ የፍተሻ ኬላዎች በተለይም የሰብዓዊ እርዳታ፣ የግብርና ግብዓት፣ መድሃኒትና ሌሎችንም አስቸኳይ ድጋፎችን ለሚያጓጉዙ አካላት ፈጣን አገልግሎት እንደሚሰጥ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ህጋዊነት ላላቸው ቁሳቁሶች ፣ ፈቃድ ላገኙ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች፣ ለረድኤት ድርጅቶች፣ ለኤምባሲዎችና ለሌሎችም በክልሉ ለሚንቀሳቀስ ፈቃድ ላላቸው አካላት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መመሪያ እንደሆነም አስረድተዋል።
የሰሜን እዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄነራል ክንዱ ገዙ በበኩላቸው መመሪያው በክልሉ ለተጎጂዎች የሚደረገውን የድጋፍ አሰጣጥ ይበልጥ ለማሻሻል የሚያግዝና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሃላፊነት መንፈስ እንዲሰሩ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.