Fana: At a Speed of Life!

“በትግራይ ክልል 150 ዜጎች በረሃብ ሞቱ ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ሀሰተኛ ነው” – የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል 150 ዜጎች በረሃብ ምክንያት እንደሞቱ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው ሲል የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለፀ።
የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በትግራይ ክልል እየቀረበ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኮሚሽነር ምትኩ በመግለጫቸው ለክልሉ እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ በተጠናከረ መንገድ እየሄደ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአገሪቱን መልካም ገጽታ የማይፈልጉ አካላት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በመጠቀም በትግራይ ክልል”በረሃብ ምክንያት 150 ሰው እንደሞተ የሚነዙት ወሬ ሀሰት ነው” ብለዋል።
ሞት ተከስቶበታል በተባለበት ኮረም አካባቢ የኦፍላ ወረዳ ቀደም ብሎ የፀጥታ ችግር አለባቸው ተብለው ከተጠቀሱት ሰባት አካባቢዎች ውስጥ የሌለ እና ከመጀመሪያው ጀምሮ የእርዳታ ስርጭቱ በተሳካ ሁኔታ የተካሄደበት ያለ ስፍራ መሆኑን መጣራቱንም አመልክተዋል።
በተደረገው ማጣራት በኦፍላ ወረዳ አንዲት እናት በህመም ምክንያት መሞታቸውን ማረጋጋገጥ መቻሉን እና ከዚህ ውጪ ግን በምግብ አቅርቦት ችግር የሞተ አለመኖሩን ተናግረዋል።
የዚህ ሀሰተኛ ዜና ዓላማ “የአገሪቱን መልካም ገጽታ ለማጉደፍ ያለመ እና መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ያላገናዘበ የራሱ ድብቅ ተልዕኮ ያለው መልዕክት ነው” ሲሉም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.