Fana: At a Speed of Life!

በቻይና በትምህርት ላይ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በቻይና በትምህርት ላይ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በትግራይ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ በኢትዮ- ሱዳን የድንበር ግጭትና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳዮች ላይ በበይነ መረብ ውይይት አካሂዷል።
በወቅቱም አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ባደረጉት ገለጻ÷ በትግራይ እየተካሄደ ባለው የህግ ማስከበር ሂደት መንግስት በአሁኑ ወቅት በትኩረት የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብና የፈራረሱ የመሰረተ ልማት አውታሮች መልሶ ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ድጋፍ ለሚሹ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ወገኖች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶች ለማዳረስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መቀሌን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የስልክና ኢንቴርኔት አገልግሎት መጀመሩን ጠቁመው÷ በሚዲያና በአንዳንድ ተቋማት ዘንድ እየቀረቡ ያሉ የተዛቡ ሪፖርቶች ተገቢነት የላቸውምም ነው ያሉት ፡፡
የቻይና መንግስት ከጅምሩ ጉዳዩ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑንና የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ አይደለም ማለቱን  አስታውሰዋል።
ከዚያም ባለፈ በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የስብዓዊ ድጋፍ ለማሳደግ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።
አምባሳደር ተሾመ አያይዘውም የኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር ግጭት በተመለከተ የተለያዩ ስምምነቶችና ውይይቶች ሲያካሂዱም መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዚህምበአውሮፓውያኑ በ1902 ሀገራቱ የደረሱት ስምምነት መኖሩን ጠቁመው÷በተለይም በ1972 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚታወቅ የሰነድ ልውውጥ ስምምነት ሁለቱ ሀገራት በያዙት ቦታ እንዲቆዩና በተከታታይ በሚደረጉ የሁለቱ ሀገራት ውይይቶች ድንበሮቹ እንዲካለሉ በተወሰነው መሰረት ሀገራቱ የጋራ የድንበር ኮሚሽን በውይይት ላይ ነበሩ ብለዋል፡፡
በዚህ ወቅት ሱዳን የሁለቱ ሀገራት የቆየ ወንድማማችነትና መልካም ጉርብትና በመጣስ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይ የተያዘችበትን አጋጣሚ በመጠቀም ድንበር ጥሳ መግባቷ የአለም አቀፍ ህግን የሚጥስ ድርጊት እንደሆነ አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
የግድቡን ጉዳይ ጨምሮ ሌሎችንም ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም ማስረዳት የሚጠበቅባቸው መሆኑን በተለይም የውስጥ ሰላማችን መታወክ ለውጭ ኃይሎች ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ሰላማችንን ለማጠናከር በጋራ መሥራት አለብን በማለት አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በቻይና የተማሪዎች ማህበር ተወካዮችም የማህበሩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ገለጻ አቅርበዋል።
ማህበሩ በሀገር ጉዳይ ሚናውን ለመወጣት በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በየዩኒቨርስቲው ያሉ የሃይድሮሎጂ ምሁራንን ለማወያየት፣ መረጃ ለመለዋወጥ፣ ችግር የሚገጥማቸውን ተማሪዎች ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመርዳት ያለውን ጠቀሜታ ገልጸዋል።
በመሆኑም በቻይና የሚገኙ ሚሲዮኖች ለማህበሩ መጠናከር ድጋፋቸው እንዳይለይ መጠየቃቸውን ቤጂንግ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.