Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ልጁን የዳረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳ ወረሞ ወረዳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ልጁን የዳረው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር ዋለ።

የሚዳ ወረሞ ወረዳ የወረሞ አጂቱ ንዑስ ወረዳ የፖሊስ አባሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌ በመጣስ ልጁን በመዳሩ ትናንት ሚያዝያ 14 2012 ዓ.ም በቁጥጥር ሥር መዋሉ ታውቋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር እሸቱ ጌታቸው እንዳሉት በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ሠርጎችን በማጥናት ሰዎች ሰርጋቸውን እንዲያራዝሙ፣ እንዲያስቀሩ ካልሆነም ደግሞ አዋጁን ሳይጥሱ በቤተሰብ ብቻ እንዲፈጽሙ ደብዳቤ ተጽፏል።

ይሁን እንጂ የፖሊስ አባሉ ሠርጉን እንዳይፈጽም በተደጋጋሚ ቢነገርም “ድግሴ ይበላሽብኛል” በማለት የልጁን ሠርግ መፈጸማቸውን አስታውቀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌ በመጣሳቸውም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የንዑስ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር በላይነህ ኃይሉ ተናግረዋል።

ፖሊሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎም በአካባቢው በርካታ ሠርጎች መቋረጣቸው ታውቋል።

“ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ የፖሊስ አባላት ሊኖራቸው የሚገባውን ቁመና ቢኖርም አዋጁን ጥሶ ድርጊቱን በመፈጸሙ በወታደራዊ ዲስፕሊን እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት ይጠየቃል” ብለዋል ኮማንደር እሸቱ።

የኮሮና ወረርሽኝ በዞኑ እንዳይስፋፋ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተላለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ለፀጥታ መዋቅሩ ግንዛቤ በመፍጠር እንዲያስከብር ጥብቅ መመሪያ መተላለፉን በመግለፅ፤ በዚህም መሠረት ሕግ የማስከበር ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን መምሪያ ኃላፊው መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.