Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞንን በህብረተሰቡና በፀጥታ ሀይሉ የጋራ ርብርብ ሰላማዊ ማድረግ መቻሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞንን የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የፀጥታ ሀይል የጋራ ርብርብ ሰላማዊ ማድረግ መቻሉ ተገለፀ።

ዞኑን የግጭት መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ለማጠፋፋት የተደረገው ሙከራ ህዝቡ ለዘመናት ባዳበረው አብሮ የመኖር እሴት እንዲከስም ማድረጉም ተገልጿል።

አባ ገዳ አህመድ መሐመድ እና አቶ አብድከሪም ኢብራሂም አሁን ላይ ስጋት ፈጥረው የነበሩ ችግሮች በህዝቡ የጋራ ትብብር ተፈተው የከሚሴ ከተማ የቀድሞ ሰላሟን አግኝታለች ብለዋል።

የከሚሴ ከተማ ከንቲባ አቶ ዑመርአስዋብ እንዳሉት፥ ህዝቡ ሰላም ወዳድና አብሮ የመኖር እሴት ለዘመናት ያዳበረ በመሆኑ በጥፋት ሀይሎች ሊደርስ የሚችለውን ጥፋት አስቀርቷል።

የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሁሴን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ ባለፉት ዓመታት ተዛብተው የቀረቡ ትርክቶች እና የሃይማኖት፣ የብሄር ብዝሃነት ተጠቅመው የጥፋት ሀይሎች ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ጥረት ማድረጋቸውን ያነሳሉ።

ከዚህ ባለፈም ከሰሜን ሸዋ ወንድም ህዝቡ ጋር የኦሮሞን ህዝብ ለማጋጨት ጥረት ቢደረግም ህዝባዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠር ተችሏል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ባሻገር የአመራር ግንኙነት በመጠናከሩ በሁለቱ ዞኖች የሚገጥሙ ችግሮች አንድ በመሆን በጋራ መፍታት መቻሉንም አንስተዋል።

የከሚሴ ከተማ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚመላለሱ በርካታ ዜጎች የሚኖሩባት ከተማ እንደመሆኗ ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴን ታስተናግዳለች።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ንግዱ ዳግም እንዳያንሰራራ እና የህብረተሰቡ የፀጥታ ስጋት እንዳይሆን ከህዝቡ ጋር በቅንጅት በመስራት ህገ ውጥ የጦር መሳሪያዎችን የመቆጣጠር ስራ በየጊዜው እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ይህም ከተማዋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖራት በማድረግ ነዋሪዎቿ የተረጋጋ ኑሮን እንዲመሩ ማገዙን አስረድተዋል።

በበላይ ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.