Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የ2012 በጀት ዓመት የካፒታል ፕሮጀክቶች 70 በመቶ ተጠናቀዋል

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል የ2012 በጀት ዓመት የካፒታል  ፕሮጀክቶች 70 በመቶ መጠናቀቁን  የክልሉ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ገለፀ።

የክልሉ የ2012 ዓ.ም የካፒታል ፕሮጀክቶች የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ውይይት ዛሬ ባህርዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡

የክልሉ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በድሉ ድንገቱ  በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት 29 የካፒታል ፕሮጀክትን ከ4 ነጥ 5 ቢሊየን ብር በላይ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የእቅዱ 70 በመቶ  መከናወኑን ገልፀዋል።

በአንጻሩ የጤና፣ የመንገድ ግንባታ እንዲሁም 72 የሚሆኑ የአነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች የአፈፃፀም ደረጃቸው ዝቅተኛ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ዝቅተኛ አፈፃፀም ለታየባቸው የካፒታል ፕሮጀክቶች የፊዝካልና የካፒል በጀት አቀናጅቶ በዕቅድ አለመስራት እንዲሁም አስፈላጊ የሆነ ክትትልና ቁጥጥር አለማድረግ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ የሆኑ የካፒታል ፕሮጀክቶች በ2013 ዓ.ም የሚሰሩእንደሆነም ኮሚሽነሩ አንስተዋል።

የክልሉ ርዕስ መስተዳድር የመሰረተ ልማት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ደሳለኝ አስራደ በበኩላቸው የ2012 በጀት አመት የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ከ2011 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም አለው ብለዋል።

ይህም ካለፉት አመታት የተሻለ የፕሮጀክት ስራ አሰራር የአመራር ስርዓት በመፈጠሩ የመጣ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጅ አሁንም ቢሆን የፕሮጀክት የአመራር ስራው የጥራት፣ ጊዜና ሀብትን በአግባቡ መጠቀም ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት አማካሪው ጠቁመዋል።

እንዲሁም የግብዓት አቅርቦት እጥረት እና የኮሮና ቫይረስ  ወረርሽኝ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አንስተዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.