Fana: At a Speed of Life!

በአሜሪካ የሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ወደ አመጽ እየተቀየሩ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ የተጀመረው ተቃውሞ ወደ አመጽ እየተቀየረ ነው ተባለ።

የተቃውሞ ሰልፉ መበራከቱን ተከትሎም አሁን ላይ በ40 ከተሞች ሰዓት እላፊ ታውጇል።

ህዝቡ ግን ሰዓት እላፊውን ችላ በማለት አሁንም ተቃውሞውን እያሰማ ነው ተብሏል።

በዚህ ሂደትም በርካታ የፖሊስ ተሽከርካሪዎች የተቃጠሉ ሲሆን በተለያዩ ሱቆች ላይም ዝርፍያ ተፈጽሟል ነው የተባለው።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በኒውዮርክ፣ ቺካጎ፣ ፊላደልፊያ እና ሎስ አንጀለስ ከተማ ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።

በፊላደልፊያ እና ሳንታሞኒካም ሰልፈኞች መደብሮችን ሲዘርፉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ተለቋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕም ህግና ስርአት እንዲከበር ካልሆነ ግን ልዩ ሃይሉን አዘምታለሁ ሲሉ አስጠንቀቀዋል።

ጆርጅ ፍሎይድ ባለፈው ሰኞ በፖሊሶች ከተያዘ በኋላ አንደኛው የፖሊስ አባል አንገቱን በጉልበቱ ተጭኖት በአሰቃቂ ሁኔታ ህይዎቱ ማለፉ ይታወሳል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህም ግድያውን የሚያወግዙ ተቃውሞዎች በመላ አሜሪካ እየተደረጉ ሲሆን፥ በአንዳንድ የአውሮፓ ሃገራትም ሰልፉ ተደርጓል።

በወቅቱ ፖሊስ ከአንድ መደብር ጆርጅ ፍሎይድ በሃሰተኛ 20 ዶላር ተገበያይቷል በሚል የደረሰውን የስልክ ጥሪ ተከትሎ ጆርጅ ፍሎይድ ከነበረበት ተሽከርካሪ እንዲወጣና ወደ ፖሊስ ተሽከርካሪ ለመውሰድ መሞከሩን ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በነበረው ሂደት የ46 አመቱ ፍሎይድ የፖሊስን ትዕዛዝ ለመፈጸም አንገራግሯልም ነው ያለው ፖሊስ።

ከዚያ በኋላም ፖሊሶች ፍሎይድን እጁን በካቴና አስረው ወደ አንድ ጥግ ወስደው ሲያናግሩትና ከደቂቃዎች በኋላም ቾቪን የተባለው የፖሊስ አባል ወደ ስፍራው ደርሶ መሬት ላይ ሲጥለውና ለበርካታ ደቂቃዎች አንገቱ ላይ ጉልበቱን ጭኖ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ተለቋል።

በዚህ ሂደት ያሰማው ተማፅኖ ሰሚ ያጣው ፍሎይድ ህይዎቱ አልፏል።

ይህን ተከትሎ ገዳዩ ዴሪክ ቾቪንን ጨምሮ አራት ፖሊሶች ከስራቸው መሰናበታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ቾቪን በ3ኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።

የፍሎይድ ቤተሰብ ጠበቃ በበኩሉ የፖሊስ አባሉ ግድያውን “ሆን ብሎና አቅዶ” ነው የፈጸመው በማለት በ1ኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል እንዲከሰስ ጠይቋል።

ጠበቃው “ፖሊሱ ድርጊቱን አቅዶ መፈጸሙን የሚያሳዩ ተጨማሪ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን አግንቻለሁም” ብሏል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.